ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት ሰላምን የማረጋገጥና ሀገራዊ ለውጡን የማስቀጠል ሃላፊነት አለብን- የመዲናዋ ወጣቶች

ጳጉሜ 4/2010 በአዲሱ ዓመት የሀገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ ሚደረገውን ጥረት የመደገፍና ሀገራዊ ለውጡን የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የሰላም ዋጋው ከፍተኛ በመሆኑ ቀጣይነቱንና አስተማማኝነቱን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ ወጣት ሲሳይ ደረጀ አሁን በሀገሪቱ እየታየ ባለው ለውጥ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ “በፍርሃት የቆየንባቸው ዓመታት ታሪክ በመሆናቸው እንደ አዲስ የተወለድኩ ያህል ይሰማኛል” ብሏል፡፡ ወጣቱ እንዳለው ወጣቶች ለጥፋት ተባባሪ ከመሆን ይልቅ ከሌላው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር የአካባቢያቸውንና የሀገራቸውን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መክሯል፡፡ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመተባበር የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ፣ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግና መሰል የበጎ አድራጎት ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገረው፡፡ ወጣት ጌትነት አባይነህም   ከብጥብጥ ጉዳት እንጂ ጥቅም የማይገኝ በመሆኑ ወጣቱም ሆነ ሌላው ህብረተሰብ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም ጠይቋል፡፡ በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች የሚነሱ ብጥብጦች ከግጭቱ ጀርባ ጥቅም የሚያገኙ ሰዎች የሚመሩት በመሆኑ መንግስት እነዚህን ሰዎች ሊታገሳቸው እንደማይገባም ነው አስተያየት ሰጠው፡፡ ወጣት ዳንኤል አዱኛ ደግሞ ሰላም በተለይ ለወጣቶች  መሰረታዊ ነገር በመሆኑ አዲሱን ዓመት በፍቅር፣ አንድነትና ይቅርታ ለመቀበል መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ ወጣት አምሳለ ኃይሉ እንዳለችው ወጣቶች በአዲሱ ዓመት ለውጡን ለማስቀጠል ምክንያታዊና አመዛኛኝ እንጅ ችኩል መሆን አይኖርባቸውም፡፡ ወጣት ግርማ ይፍራም አሁን እየታየ ያለውን ለውጥ ዘላቂነተ ለማረጋገጥ  አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጦ መንግሥትም ወጣቶች ከስራ እድልና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ ወጣት ተመስገን ጋዲሳ ወጣቱ ኃይል ሰላማዊ ሀገር መረከብ ይችል ዘንድ ራሱን ማብቃት እንደሚጠበቅበት ገልጾ ህብረተሰቡም ሰላሟ የተረጋገጠ  ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብሏል፡፡ በእስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና የኪነ ጥበብ ስራዎች ወጣቶችን የማቀራረብና ለሰላማቸው ዘብ እንዲቆሙ የማንቃት ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ያብራራው ወጣት ተመስገን፤ ያለፉ ስህተቶችን እየነቀሱ ከመወቃቀስ ይልቅ ሙሉ ትኩረትን ለሀገሪቱ ሰላምና ልማት መረጋገጥ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡ ወጣቶች በአዲሱ ዓመት ከስሜታዊነት ከጅምላ ፍረጃና የደቦ ፍርድ ርቀው ለተሻለ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት መስራት እንዳለባቸውም ነው የተጠቆመው፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ አዲሱን ዓመት አረጋውያንንና አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፣ 2011 የሚያስመሰግን ስራ ሰርተው ስማቸውን የሚያስጠሩበት  ስኬታማ ዓመት እንዲሆንላቸው ለወጣቶች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም