ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ የልማት ፕሮጀክቶችን አስጀመሩ

221

ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ወራት የሚጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶችን አስጀመሩ።

ከንቲባዋ በዛሬው እለት ያስጀመሯቸው የልማት ፕሮጀክቶች አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ 4 ባለ 9 ወለል ሕንጻዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣የምገባ ማዕከል ግንባታና የከተማ ግብርና ይገኙበታል።

እንዲሁም በክፍለ ከተማው ወደ 200 የሚሆኑ ቤቶችን በክረምት በጐ ፈቃድ የማደስና የዳቦ አቅርቦትን ለማሳደግ የሚያስችል መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካ ግንባታም ከተጀመሩት ፕሮጀክቶች መካከል ናቸው።

በ3 ወር ለሚሰራው የጋራ መኖሪያ ቤትና የምገባ ማዕከል ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በፕሮጀክቶቹ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ እንደገለጹት፤በክፍለ ከተማው በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውስጥ የነዋሪውን አንገብጋቢ ችግሮች በመለየት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ይሰራሉ።

በእነዚህ ጊዜያትም መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት በተመረጡ ክፍለ ከተሞችና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነዋሪዎች ላይ ለውጥ በማምጣት እንደማሳያ በመሥራት በቀጣይ የማስፋፊያ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተገጣጣሚ የግንባታ ቴክኖሎጂ በ3 ወር ውስጥ የሚጠናቀቅ ባለ 9 ወለል 4 ሕንፃዎች ለ200 ነዋሪዎች የሚገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአንድ ጊዜ የሁሉንም ነዋሪዎች ችግር መቅረፍ ባይቻልም በተመረጡ አካባቢዎች በመሥራትና ውጤት በማምጣት የማኅበረሰቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከተማዋ የዲፕሎማቲክ ማዕከል ሆና ደረጃዋን የጠበቀች፣በውበቷና በፅዳቱም ማራኪ እንዲሆኑ በማስቻል በቅርቡ የተጀመሩ የከተማዋን ደረጃ የሚያሳድጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አብራርተዋል።

May be an image of 6 people, people sitting and people standing

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኃላፊ አቶ ጀማል አሕመድ፤ሚድሮክ ለድርጅቱ ሁለተኛ የሆነ የምገባ ማዕከል ግንባታና በክፍለ ከተማው ዛሬ ከተጀመሩት 4 ህንፃዎች አንዱን የሚገነቡ መሆኑን ገልፀዋል።

ኩባንያዉ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተቀብሎ በልማቱ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤በቀጣይም ከመንግሥት ጎን ሆኖ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ኃላፊ አቶ ደርቤ አሰፋው በበኩላቸዉ፤ ድርጅቱ የኮርፖሬት ሃላፊነቱን ለመወጣት በተለያዩ መስኮች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደምም የተማሪዎች ምገባን ጨምሮ በሌሎችም በከተማዋ በሚደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱንም ጠቁመዋል።

አሁን ላይም አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚገነባው ህንጻ አንዱን ለመገንባት ቃል ገብተዋል።የዳቦ አቅርቦትን ማሻሻል፣ማዕድ ማጋራትና ምገባን ማስፋፋት፣የከተማ ግብርናን ማስፋፋት፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣የቤቶች ግንባታና እድሳት የመሳሰሉት በትኩረት የሚሰራባቸው ሆነው ተለይተው ወደ ተግባር መገባቱ ተገልጿል።

አጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ በበጎ ፍቃደኛ ተቋማትና ባለሃብቶች ትብብር፣ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክና በሌሎችም ባለሃብቶች ተሳትፎ የሚሰሩ መሆናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም