ለኢትዮጵያዊነት እሴት መጎልበትና የአብሮነት ጽናት የኪነ-ጥበብ ሚና የላቀ በመሆኑ በልዩ ትኩረት መሰራት አለበት

123

ግንቦት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያዊነት እሴት መጎልበትና የአብሮነት ጽናት እና በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመገንባት የኪነ-ጥበብ ሚና የላቀ በመሆኑ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አንጋፋው የኪነ-ጥበብ ሰው ተስፋዬ ሲማ ተናገረ።

የተዘጉ ቴአትር ቤቶችን መክፈት፣ የኪነ-ጥበብና ግብረገብ እሴቶችን በትምህርት ሥርዓቱ ማካተት፣ ለኪነ- ጥበብ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶችን መደገፍ መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል።

አንጋፋው የኪነ-ጥበብ ሰው ተስፋዬ ሲማ፤ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት ትምህርት ነበር በማዕረግ ያጠናቀቀው።

በወጣትነቱ በአርሲ ክፍለ ሀገር በቴአትር ክፍል ኃላፊነትና በአዲስ አበባ ባህልና ስፖርት ቢሮ የኪነ-ጥበብ ክፍል ኃላፊነት የሰራ ሲሆን በአዲስ አበባ የቴአትርና የሙዚቃ ክበባት እንዲመሰረቱ ሚናው ጉልህ ነበር።

በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ደማቅ አሻራ የነበረው ባለታሪኩ በብሔራዊ፣ በሀገር ፍቅር፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ፣ በራስ ቴአትር በተዋናይነትና በአዘጋጅነት እንዲሁም በሬዲዮና ቴሌቪዥን ድራማና በፊልም ሥራዎቹ ብቃቱን አሳይቷል።

የቴአትርና ሥነ-ጽሑፍ ማሰልጠኛ ማዕከል በመክፈት ለተከታታይ አምስት ዓመታት ከትምህርት ቤቶቹ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች መልምሎ በማሰልጠን ዛሬ ላይ በኪነ-ጥበቡ ዓለም አንቱ የተሰኙ ከያኒያንን አፍርቷል።

በአገርኛ እሴቶች ከላይ ያጠነጠኑ የፀጋዬ ገብረመድህን ድርሰት ሥራዎችን በመጫወት አድናቆትን ያተረፈው ተስፋዬ ሲማ "በኪነ-ጥበብ ጠሉ ሕወሓት ጥርስ ተነክሶበት" በመጨረሻም ከአገር እንዲሰደድ ተደርጓል።

ከ22 ዓመታት በላይ የውጭ ቆይታው ግን በግሉና ከጣይቱ የኪነ-ጥበብና የትምህርት ማዕከል ጋር በመሆን ከ200 በላይ ቴአትሮችን በመጻፍ፣ በማዘጋጀትና በመተወን በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ በአውሮፓና ሌሎች አገራት ተዘዋውሮ አቅርቧል።

በወጣትነቱ ያሰለጠናቸው ተማሪዎች ትልቅ ደረጃ ይደርሳሉ በሚል ሳይሆን ለቴአትር ጥበብ ሙያ ጥማቱን ለማርካት እንደነበር ገልጾ፤ ተማሪዎቹ በኪነ-ጥበቡ እየተጫወቱት ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጿል።

በቅርቡ ወደ አገር ቤት የተመለሰው አርቲስቱ ኢትዮጵያን ለማዳን አንዱ ቁልፍ መሳሪያ ኪነ-ጥበብ እንደሆነ ያምናል።

በሕወሓት ዘመን የኪነ-ጥበብ ተቋማት እንዲዳከሙ፣ የታሪክ ትምህርት እና አገራዊ  የመከባበር እሴቶች እንዲጠፉ መደረጉን ገልጾ፤ የኪነ-ጥበቡ መውደቅም ለዛሬ ኢትዮጵያዊነት መውደቅ ጋር ያያይዘዋል።

የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት፣ የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት፣ የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ፣ ራስ ቴአትርን ጨምሮ አብዛኞቹ ሥራ ማቆማቸው እንዳሳዘነው ይገልጻል።

ኢትዮጵያዊነት፣ አገራዊ አንድነት፣ አብሮነት እንዲጸና፣ ትውልድ በስነ-ምግባር እንዲታነጽ የኪነ-ጥበብ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጿል።

የተዘጉ ቴአትር ቤቶችን መክፈት፣ የኪነ-ጥበብና ግብረገብ እሴቶችን በትምህርት ሥርዓቱ ማካተት፣ ለኪነ-ጥበብ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች መደገፍ የቀጣይ ትኩረት መሆን አለበት ብሏል።

ባለሙያዎቹም ከሕዝብ ፊት ቀድመው ስለ ኢትዮጵያዊነት እየተጠበቡ አገርን ወደፊት ማራመድ፣ ኪነ- ጥበብን ለጥበብ ብቻ ሳይሆን ለማስተማሪያነት መጠቀም ግዴታ አለባቸው ብሏል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ተደራሽ እንዲሆኑ በትጋት እየሰራ የሚገኘው አርቲስቱ በጥበብ ድግሱ እንዲቀጥል እንደሚሰራ አረጋግጧል።

በውጭ በሚገኙ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ምቹ ባልሆነ ሁኔታም በመሰባሰብ ክውን ጥበባትን በተለያዩ ክፍላተ ግዛቶች ተደራሽ በማድረግ የሙያ ጥማታቸውን ለማርካት እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል።

በውጭ አገራት የሚወለዱ ልጆች ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እንዲያዳብሩ በኪነ-ጥበብ ከማስተማር ባለፈ ወላጆች ወደ አገር ቤት እየወሰዱ ማሳየት ቢችሉ መልካም መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም