መቀሌ ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለአንድ ተለያዩ

59
መቀሌ ግንቦት 10/2010  በትግራይ ስታዲዮም ዛሬ ተስተካካይ ጨዋታ ያደረጉት መቀሌ ከነማና ቅዱስ ጊዮርጊስ  አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተለያዩ። መቀሌ ከነማ ከእረፍት መልስ በ72ኛው ደቂቃ ላይ 11 ቁጥሩ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመሃል ያገኛትን ኳስ ክለቡን ቀዳሚ የምታደርግ ኳስ ሊያስቆጥር ችሏል። ጊዮርጊሶች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት በመቻላቸው በ82ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው 21 ቁጥሩ ዓብዱልከሪም ዛኪ አክርሮ የመታትን ኳስ የግቡ ቋሚ የመለሳት ሲሆን በመቀሌ ተከላካዮች የነበረውን ክፍተት ተጠቅሞ 2 ቁጥሩ ዓብዱልከሪም መሓመድ አክርሮ በመምታት ግብ በማስቆጠር ቡዱኑን ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አስችሎታል። መቀሌ ከነማ በማጥቃት ላይ ተመስርተው የጀመሩት ጨዋታ ከሶስት በላይ ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶች በጊዮርጊሱ በረኛ ሊከሽፉ ችለዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ወደ ማጥቃት ተሸጋግረው ያካሄዱትን ጨዋታ በመቀሌ ከነማ ላይ የበላይነት ሊይዙ የቻሉ ሲሆን በተለይም በመሃል ክፍሉ የታየውን መሳሳት ተደጋጋሚ ወደ ግብ ሙከራ ሊሄዱ አስችሏቸዋል። ጊዮርጊሶች በ16ኛው፣ በ22ኛው፣ በ34ኛውና በ50ኛው ደቂቃዎች ላይ ጥሩ የግብ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በመቀሌ ከነማ በኩልም በ18ኛው፣ በ21ኛውና በ81ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ሙከራዎች አድርገዋል። መቀሌ ከነማ ሁለት የማአዘን ምቶች ያገኘ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ አምስት አግኝቷል። የመሃል ዳኛው ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ አልፎ አልፎ ከመስመር ዳኞች ጋር ያለመናበብ ችግር የታየባቸው ሲሆን በአብዛኛው ጨዋታው በተሻለ ሁኔታ መርተውታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም