ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣለን---የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች

ዲላ፤ ግንቦት 11/2014 (ኢዜአ)፡ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ሰላማቸውን በዘላቂነት ለማስጠበቅ እንደሚሰሩም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል መምህር ብዙነህ ደመቀ የሀገር ሰላምና አንድነት እንዲጠናከር ልዩነቶችን በውይይት ማጥበብ አስፈላጊ በመሆኑ ለእዚህም እየሰራን ነው ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖትና የብሔር መልክ ያላቸው ግጭቶችን በመፍጠር ሀገርን ለማተራመስና ህዝብን ሰላም ለመንሳት  የሚደረግ ጥረትን እንደማይቀበሉ ተናግረዋል።

አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በውይይት በመፍታት የኢትዮጵያን መውደቅ የሚመኙ ሃይሎችን እኩይ ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

"ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ አለመግባባቶችን በመፍታት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የበኩሌን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

የምክክር መድረኩ አሁን እየተስተዋሉ ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ ሼህ መሐመድ ከማል የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።

 ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት እንዳትወጣ ልዩነቶችን በማጉላትና የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን በማንሳት ለሚደረግ ጥረት ተባባሪ ባለመሆን ለሰላምና ለአብሮነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።  

"ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ይዞት የሚመጣውን ዕድል ሁላችንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል"ያሉት ነዋሪው፤ ለሀገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ሀገራዊ ልማትና ብልጽግና እንዳይመጣ የሚጥሩ የጥፋት ሃይሎችን አጀንዳ በማክሸፍ ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም እንደሚሰሩም ሼህ መሐመድ ገልጸዋል።

"ሀገራዊ የምክክር መድረኩ እርስ በርስ የማያግባቡ ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ዕድል ስለሚፈጥር መጪውን ጊዜ የተሻለ አንዲሆን በመድረኩ በመሳተፍና ገንቢ ሀሳብ በመስጠት ሃላፊነቴን እወጣለሁ" ብለዋል።

ለችግሮች በውይይት መፍትሄ ለማምጣት ከታች ጀምሮ ሊዳብር እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ወንጌላዊ ብርሃኑ ጌዴቾ ናቸው።

ሀገራዊ የውይይት መድረኩ ምቹ መደላድል ይፈጥራል የሚል አምነት እንዳላቸው ገልጸው ለስኬታማነቱ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ሀገራዊ አንድነት እንዲረጋገጥ ሁሉም ለሀገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማነት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሥራቸው የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች በሀገራዊ የምክክር መድረኩ በንቃት በመሳተፍ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ከወዲሁ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም