በየደረጃው የሚገኘው አመራር የአለምን፣ የአገር እና የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳት አገርን ለማሻገር መስራት ይጠበቅበታል

ድሬዳዋ፣ ግንቦት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በየደረጃው የሚገኘው አመራር የአለምን፣ የአገር እና የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳት አገርን ለማሻገር መስራት እንደሚጠበቅበት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አስገነዘቡ።

‘አዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ - አዲስ አገራዊ እምርታ’ በሚል መሪ ሃሳብ ለድሬዳዋ ከፍተኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በየደረጃው የሚገኘውን አመራር አቅም በየጊዜው በመገንባት የአገርን ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚገባ በስልጠናው ላይ የተሳተፉት የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ና ብልፅግናዋን ዕውን ለማድረግ በየጊዜው የአመራሩን አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤ አመራሩ የዘመኑን ቴክኖሎጂና እና ዕውቀት መላበስ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም በየደረጃ የሚገኘው አመራር የአለምን፣ የአገር እና የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታዎች መረዳት አለበት ብለዋል።

ስልጠናው የአገርንና የአስተዳደሩን ነዋሪዎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ነው ከንቲባ ከድር የገለፁት።

በሚቀጥሉት ቀናት በአገሪቱ የ10 አመታት መሪ ዕቅድ፣ በሚዲያ በኮሙኒኬሽን፣ በብልፅግና ፓርቲ ተቋማዊ ጥንካሬ ላይ ስልጠና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም