የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኛ ሆኖ መደራጀት አለበት - ጋዜጠኞችና ጦማሪያን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኛ ሆኖ መደራጀት አለበት - ጋዜጠኞችና ጦማሪያን
አዲስ አበባጳጉሜ 3/2010 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተጣለበትን ሰብዓዊ መብት የማስከበር ተግባር በወጉ ለመወጣት ከመንግስት ገለልተኛ ሆኖ መደራጀት አለበት ሲሉ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ተናገሩ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ ተደራሽ ከመሆን ችግር ውጪ ከመንግስት ተፅዕኖ የሌለበት ተቋም መሆኑን ይገልጻል። ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 210/1992 ሲቋቋም በህገ-መንግስቱ ሰብዓዊ መብት ተብለው የተደነገጉትን ለማስከበርና የመብት ጥሰቶች እንዲታረሙ በመንግስት ላይ ጫና የማድረግ ኃላፊነትን በማንገብ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ኮሚሽኑ የተጣለበትን ይህንን ከፍተኛ ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ገልፀዋል። "ዞን ዘጠኝ" በሚል የሚታወቁት ጦማሪያን አባል የሆኑት አቤል ዋቤላ እና በፍቃዱ ኃይሉ በተለይም በእስር ቤቶች አካባቢ የሚታየው የታራሚዎች አያያዝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚስተዋልበት መሆኑን የራሳቸውን ተሞክሮ በመጥቀስ ይናገራሉ። ጦማሪያኑ እንደሚሉት በእስር ቤት ቆይታቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈፀመባቸው ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አቤት ቢሉም ተገቢውን ምላሽ አላገኙም። ጦማሪ አቤል ዋቤላ “እኔና ጓደኞቼ ታስረን ቂሊንጦ በነበርንበት ጊዜ፣ ማዕከላዊ በነበርንበት ጊዜ አመልክተናል፤ በዝርዝር በምን አይነት ቀንና ሁኔታ፤ የትኛው አካል ምን አይነት ጥሰት እንዳደረሰብን ገልፀው ቤተሰቦቻችንና የህግ አማካሪዎቻችን አመልክተዋል፤ ግን ኮሚሽኑ ያንን ለመፍታት ምንም እንቅስቃሴ አላደረገም'' በማለት ገልጸዋል፡፡ በፍቃዱ ኃይሉ በበኩላቸው እንደገለጹት "በ2008 ዓ.ም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት በድጋሚ ታስሬ አዋሽ ሰባት ካምፕ ውስጥ ተወስጄ ነበር፤ ከብዙ እስረኞች ጋር ሁላችንም ከፍተኛ የማሰቃየት ተግባር ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ደርሰውብናል፤ ነገር ግን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዳላየ ነው ያለፈው ነው”፡፡ ጋዜጠኞቹ ፍሬው አበበ፣ ታደሰ ዳኛቸውና ታምሩ ፅጌም ተመሳሳይ ትዝብት ይጠቅሳሉ። በተለይም ማረሚያ ቤቶች አካባቢ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀም በተደጋጋሚ መታዘባቸውን ጋዜጠኞቹ ገልፀዋል። ኮሚሽኑ ለፍርድ ቤቶችም ሆነ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርበው ሪፖርት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በሚያስጠብቅ መልኩ የተቃኘ እንዳልሆነም ያብራራሉ። ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ያህል ላለመስራቱ ከመንግስት ወይም ከአስፈፃሚው አካል ነፃ አለመሆኑን እንደምክንያት ጠቅሰዋል። ኮሚሽኑ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የዜጎችን ሰብአዊ መብት ማስጠበቅ ይችል ዘንድ እውነተኛ፣ ከወገንተኝነት የፀዳ አደረጃጀት ሊፈጠርለት እንደሚገባ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለፁት። ኮሚሽኑ ከሌሎች ሲቪል ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት የሚችልበት ነፃ አደረጃጀት ሊኖረውና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎችም መዋቀር አለበት ብለዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ በበኩላቸው ተደራሽ ከመሆን ችግር ውጪ ከመንግስት ተፅዕኖ የሌለበት ነፃ መስሪያ ቤት ነው ሲሉ ይከራከራሉ። ለአብነትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰቱ ግጭቶች የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን ለማጋለጥ ያደረገውን ጥረት ያነሳሉ። በተለይም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች አማካኝነት የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሰፊ ስራ መሰራቱን ይጠቅሳሉ። የምርመራ ግኝቶቹም መንግስትን ተጠያቂ የሚያደርጉ እንደነበሩ በመግለፅ ተቋሙ ተደራሽ ከመሆን ችግር ውጪ ከመንግስት ተፅዕኖ የሌለበት ነፃ መሆኑን ተናግረዋል። "ኮሚሽኑ ማንኛውም ጥቆማ ከደረሰው ምርመራ አድርጎ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ያደርጋል፤ ጥሰቶች እንዳይፈፀሙ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተለመከተ ለተቋማት ላይ የግንዛቤ መስጠት ስራ በሰፊው ይሰራል" በማለትም ያብራራሉ። በኮሚሽኑ ሥራ ላይ እንቅፋት የሆነውን ተደራሽነት ለመፍታትም በሰው ኃይል የተደራጁ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን ለመክፈት የሚያስችል አዲስ አደረጃጀት ከመጪው መስከረም 2011 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደረግ አቶ ደምሰው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ኃላፊነት መምጣቱን ተከትሎ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች በቀረቡ ዘገባዎች ላይ በተለይ በማረሚያ ቤቶች ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ይፋ መደረጉ ይታወቃል።