ዩኒቨርስቲው በአዲስ አበባ ከተማ በቅርስነት የተመዘገቡ ሃብቶች ላይ የሚሰራ ማዕከል ሊያቋቁም ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርስቲው በአዲስ አበባ ከተማ በቅርስነት የተመዘገቡ ሃብቶች ላይ የሚሰራ ማዕከል ሊያቋቁም ነው
ግንቦት 10/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በአዲስ አበባ ከተማ በቅርስነት የተመዘገቡ ሃብቶች ላይ የሚሰራ ማዕከል ሊያቋቁም መሆኑን ገለፀ።
የዩኒቨርስቲው የማሕበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ የመሰረተበትን 6ተኛ ዓመት አስመልክቶ በመዲናዋ በቅርስነት የተመዘገቡ ሃብቶችን የሚያሳይ 'የፎቶ አውደ ርዕይ' ለእይታ አቅርቧል።
በአውደ ርዕዩም በመዲናዋ ያሉ የቀድሞ አብያተ-መንግሥትና የመኳንንት ቤቶች፤ ቤተ-ዕምነቶች፤ ለልዩ ልዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች የተገነቡ ቤቶችና የውጭ ሀገር ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ፎቶ ለዕይታ ቀርበዋል።
የዩኒቨርስቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ተሾመ፤ ቅርሶችን መጠበቅ የሚጀመረው አስቀድሞ የማስተዋወቅ ስራን በማከናወን ነው ብለዋል።
በመሆኑም ዩኒቨርስቲው በመዲናዋ የሚገኙ የተመዘገቡ ቅርሶችን የሚያስተዋወቅ፣ ጥናትና ምርምር የሚያደርግና ቅርሶች ላይ የሚሰራ ማዕከል ሊያቋቁም መሆኑን አስታውቀዋል።
ማዕከሉ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ የሚቋቋም ሲሆን በኪነ-ሕንፃ ጥበብና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች ላይ ምርምርና ጥናት እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
እስካሁን በመዲናዋ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በቅርሶች ላይ በቂ ጥናት የሚያካሔዱ ማዕከሎች ባለመኖራቸውም ማዕከሉን ለማቋቋም መታቀዱን አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከከተማዋ ባህል፣ ኪነጥበባትና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበርም በመዲናዋ ያሉ ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸውና ነባር ይዞታቸውን ሳይለቁ እንዲታደሱ ለማድረግም እንደሚሰራ ገልፀዋል።
''በአግባቡ ቅርሶች ላይ የመስራት ተግባር የትምህርት ተቋማት ጭምር ኃላፊነት እንደሆነም'' ተናግረዋል።
"ቅርስ በትውልዶች መካከል ያለውን ቁርኝት የሚያሳይ የወርቅ ሰንሰለት ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይም ተመሳሳይ የፎቶ አውደ-ርዕይ የመዲናዋ ነዋሪዎችን ባማከለ ቦታ ላይ ለዕይታ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል።