ቀጥታ፡

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት በግልጽ ሊያወግዝ ይገባል

ግንቦት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት በግልጽ ሊያወግዝ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ ፡፡

የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች አሸባሪው ህወሃት በትግራይ ክልል በአስገዳጅ ሁኔታ ከታዳጊ እስከ አዛውንት ለጦርነት እየመለመለ እንደሆነ በማጋላጥ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መንግስትም የአሸባሪ ቡድኑ ዳግም ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም በተግባራዊ እርምጃዎቿ እያሳየች መሆኗን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ፣  ሰብዓዊ ዓላማ ያለው የተኩስ ማቆም መደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ በመንግስት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎችን በዚህ ረገድ በአብነት አንስተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ከቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፣ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞችና ሌሎችም ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጋር በሰላም ጉዳይ ላይ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስት አሁንም ለሰላም ያለውን አቋም የሚያሳዩ ግልፅ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ለተለያዩ የዓለም ማህበረሰብ አካላት የማስረዳቱ ስራ ቀጥሏል ነው ያሉት።

ሆኖም ኢትዮጵያ ለሰላም በርካታ ርቀቶችን ብትጓዝም አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን የህወሃትን የዳግም ጦርነት ዝግጅትና የታጣቂ ምልመላ በትክክል ተገንዝቦ  በቡድኑ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ለጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅትና የአስገዳጅ የታጣቂ ምልምላ እንዲያቆም በጠንካራ አቋም ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም