ተመሳስለው ከውጭ የሚገቡ የአገር ባህል አልባሳት ለአገር ውስጥ ገበያ ስጋት ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ተመሳስለው ከውጭ የሚገቡ የአገር ባህል አልባሳት ለአገር ውስጥ ገበያ ስጋት ሆነዋል
አዲስ አበባ ጳጉሜ 3/2010 ከኢትዮጵያ የባህል አልባሳት ጋር ተመሳስለው ከቻይና የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ገበያ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የባህል ልብስ አምራቾችና ሻጮች ገለፁ። ምርቶቹ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል። ኢትዮጵያውያን በአለምአቀፍ ደረጃ ከሚታወቁበትና በቀላሉ ከሚለዩበት ነገሮች ውስጥ ባህላዊ አልባሳት ዋነኞቹ ናቸው። በተለይም ዘመን መለወጫን የመሳሰሉ በዓላት ሲከበሩ አቅሙ የፈቀደለት አዲስ የአገር ባህል ልብስ በመግዛት እጅ ያጠረው ደግሞ የክቱን አውጥቶ በመልበስ በዓሉን በደስታ ማክበር የተለመደ ነው። ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች የአገር ባህል አልባሳትን በአዘቦት ቀንና በስራ ቦታ መልበዝ ያልተለመደ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በዲዛይንና በውበት እየተሻሻሉ መመረት በመጀመራቸው የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቀዳሚ ምርጫ እየሆኑ መጥተዋል። ይሁንና አልባሳቱ በከፍተኛ ልፋት በእጅ የሚሰሩ ከመሆናቸው ባለፈ አልባሳቱን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ዋጋ መጨመር የልብሶቹን ዋጋ የማይቀመስ አድርጎታል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ከባህላዊ አልባሳቶቹ ጋር የሚመሳሰሉ ጨርቆች ከቻይና በብዛት በመግባት የሸማ ገበያውን እየተቆጣጠሩ በመሆኑ በገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ስለመሆኑ ኢዜአ ያነጋገራቸው አምራቾችና ነጋዴዎች ተናግረዋል። ነጋዴ አቶ በላይ ንጉሴ እንዳሉት የቻይናው አልባሳት ምርት በዋጋም ቅናሥ በመሆኑ የሀገር ባህል ልብሶች ከገቢያ ወቅጭ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ አክለውም ይሄ ከንግስተ ሳባ ጀምሮ የሚታወቅ የኢትዮጵያ ኩራት የሆነውን ገበያውን እየረበሸና ባህሉን እያበላሸ ያለውን የቻይና ምርት መንግስት ማሰብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አምራችና ነጋዴ የሆኑትአቶ አዶሌ ወራሽ በበኩላቸው “ቻይናዎች በፋብሪካ ነው የሚሰሩት፤ እኛ በእጃችን እያንዳንዷን የድር አይኗን ለቅመን ፈልቅቀን የምንሰራው ስራ ስለሆነ የእነርሱ አንዴ ፋብሪካ ውስጥ ገብቶ ታትሞ በጣም ብዙ ምርት ያመርታሉ፤ ከዚህ የተነሳ በርካሽ ዋጋ ያቀርባሉ፤ያውም ጥራቱ እንደኛ አይደለም ሲታጠብ የታተመው ስለሆነ ይለቃል”ስሉ ገልጸዋል፡፡ ከውጭ ተመሳስለው የሚገቡት ምርቶች የአገር ወስጥ ገበያውን ከማቀዛቀዝ ባለፈ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያበላሽ መሆኑንም የባህል አልባሳት አምራቾችና ተጠቃሚዎች ተናግረዋል። ህብረተሰቡ የአገሩን ትክክለኛ ምርት በመጠቀም ባህሉን መጠበቅ እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት። “ኢትዮጵያን የምናስተዋውቅበት አርማችን ነው ስለዚህ ይሄ ስራ ወደፊት በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ቻይና የምትቀጥል ከሆነ የስራው ደብዛ ይጠፋል፤በዚህ ደረጃ የምትታወቀው አገራችን ዕውቅናውን ታጣለች'' ያሉት ደግሞ አምራችና ነጋዴአቶ አዶሌ ወራሽ ናቸው፡፡ የባህል አልባሳቱ ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ ምርቶች ከቻይና ከሚመጣው እጅግ የተሻለና በብዙ ድካም ጊዜ ተወስዶ የሚመረት መሆኑን ጠቅሰው የባህል አልባሳቱ ወደአገር እንዳይገቡ ማድረግ የሚያስፈልግ እንደሆነ ጠቁመዋል። የባህል አልባሳት ነጋዴዎችም ህብረተሰቡ ትክክለኛውን የባህል አልባሳት እንዲጠቀም ከቻይና የሚገባው ምርት መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል። በሽመና ስራው ላይ የተሰማሩ በርካቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ምርቱ በፋብሪካ ተመርቶ ወደአገር እንዲገባ በመደረጉ የዜጎችን የስራ ዕድል የሚጎዳ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ከባህል አልባሳት ጋር ተመሳስለው ከቻይና የሚገቡ ምርቶች የባህል ኢንዱስትሪውን ወደ ኋላ ከመጎተት ባለፈ የዜጎች ተጠቃሚነትን የሚያሳጣ ነው ይላሉ። እንደ አቶ ገዛሃኝ ገለጻ፤ ባህላዊ አልባሳት ብቻ ሳይሆን ለውጭ አገር ዜጎች ለስጦታ የሚሸጡ መስቀልን ጨምሮ የኢትዮጵያ መለያ ቁሳቁሶች ጭምር በቻይና ኮፒ ተደርገው መልሰው ለአገር ወስጥ ገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ። አለምአቀፍ የንግድ ስምምነትና የህግ ማዕቀፍ በሌለበት ሁኔታ ምርቶቾ ወደ አገር እንዳይገቡ ማድረግ የማይቻል መሆኑንም አንስተው ችግሩን ለመፍታት የአገር ባህል ልብስ አምራቾች በብዛትና በጥራት እንዲያመርቱና የህብተሰቡን የመግዛት አቅም ባገናዘበ ዋጋ እንዲሸጡ ድጋፍና ክትትል የሚደረግ መሆኑንም አስታውቀዋል። የባህል ኢንዱስትሪውን የበለጠ በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማስቀረት ላይ አጥጋቢ ስራ እንዳልተሰራ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ የባህል ኢንዱስትሪ ፖሊሲው የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ወደ ስራ ለማስገባት የአሰራር ስርዓት እንደሚዘረጋ ጠቁመዋል።