ከአሜሪካ ጋር በ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች ዙሪያ ውይይት ማድረጉን መንግስት ገለጸ

77

ግንቦት 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት ከአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናትና የሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ጋር በ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች ዙሪያ ውይይት ማድረጉን ገለጸ።

ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጽድቁ ለማድረግ የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን አመልክቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ሰባተኛ መደበኛ ስብሰባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2014 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በዘጠኝ ወራቱ በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብትና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያን መጉዳት አላማ ያደረጉ ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች በተወሰኑ የአሜሪካ የሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት መዘጋጀታቸውንና ሕጎቹ እንዳይጽድቁ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የረቂቅ ሕጎቹን አደገኛነት እንዲሁም በኢትዮጵያና በአሜሪካ ግንኙነት የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ የሚያስረዱ ጽሁፎች ለአሜሪካ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች መሰራጨቱን ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ለአሜሪካ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የሕጎቹን ጎጂነት የተመለከተ ደብዳቤ መጻፋቸውንም አመልክተዋል።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን ቡድን ወደ አሜሪካ በማቅናት በረቂቅ ሕጎቹ ዙሪያ ከአገሪቷ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊዎችና ከሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ከኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች ጋር ውይይት ማድረጉን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

የልዑካን ቡድኑ አባላት ሕጎቹ አሉታዊና የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑን እንዳብራሩም አመልክተዋል።

በተለይም ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የያዙትን አቋም ዳግም እንዲያጤኑና ሕጎቹ የአገራቱን የጋራ ጥቅም የማያስጠብቁ መሆናቸውን እንዲረዱ የማድረግ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

ለውይይቶቹ መሳካት በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የነበራቸው አበርክቶ ወሳኝ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁንም ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይድቁ የሚደረጉ ጥረቶች እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ‘ኤችአር 6600’ ለአሜሪካ ኮንግረስ እንዲቀርብ የተዘጋጀ ረቂቅ ሕግ መሆኑ ይታወቃል።

ከ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕግ ለአሜሪካ ሴኔት እንዲቀርብ የተዘጋጀ ነው።

‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ‘ኤችአር 6600’ የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መምራቱ የሚታወስ ነው።

‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕግ ሴኔቱ እ.አ.አ በ2022 ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት ማድረጉ ይታወቃል።

ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በየአካባቢያቸው ያሉ ተመራጮቻቸውን በአካልና በስልክ በማነጋገር፣ ደብዳቤ በመጻፍ፣ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መልዕክቶችን ቀርጾ በማስተላለፍና ሰላማዊ ሰልፎችን በማዘጋጀት ሕጎቹ ለድምፅ አሰጣጥ እንዳይቀርቡ እየሰሩ ይገኛል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም