የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ለሌላ ተግባር በመዋላቸው ተተኪዎችን ለማፍራት ተግዳሮት ፈጥሯል -- አሰልጣኞችና ታዳጊ ወጣቶች

185

ሐረር ግንቦት 9/2014 (ኢዜአ) በሐረር ከተማ የስፖርት ማዘውተርያ ሜዳዎች ለሌላ አላማ በመዋላቸው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተግዳሮት መፍጠሩን አሰልጣኞችና ታዳጊ ወጣቶች አመለከቱ።

የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎቹ ወደቀድሞ ተግባራቸው  እንዲመለሱ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን አስታውቋል።

በሐረር ከተማ በተለምዶ  የራስ መኮንን፣ አሚር ሀቡባ፣ ሚካኤል እና ፖሊስ ሜዳ ተብለው የሚጠሩ የስፖርት ማዘውተርያ ሜዳዎች ለተሽከርካሪ  መናኽርያነትና ማቆሚያነት እንዲሁም ለኮንስትራክሽን ተረፈ ምርት  ማከማቻና ለሌሎች ተግባራት የዋሉ መሆኑን አሰልጣኞችና ታዳጊ ወጣቶች ለኢዜአ ተናግረዋል።

የስፖርት ሜዳዎቹ ለሌላ ተግባር መዋላቸው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተግዳሮት መፍጠሩን ጠቁመው  የሚመለከተው አካል መፈትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የቀድሞ የከተማው እግር ኳስ ተጫዋችና የአሁኑ የታዳጊዎች ፕሮጀክት አሰልጣኝ ጌቱ ነጋሽ እንዳለው በርካታ ስመጥር ስፖርተኞችን ያፈሩት የስፖርት  ሜዳዎች ለሌላ ተግባር እንዲውሉ መደረጉ በስፖርት ባለሞያው ላይ ቅሬታ ፈጥሯል።

" ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በምናከናወነው ሰራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረብን ስለሚገኝ የሚመከለከተው አካል ችግሩን ሊፈታ ይገባል " ብሏል።

"የእግር ኳስ ስፖርቱን ማሰልጠን ስጀምር በታዳጊዎች ላይ ጥሩ መነሳሳት ነበር" ያለችው ደግሞ የሴት ታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት አሰልጣኝ ገላዬ ገበየሁ ናት ።

የስፖርት ማዘውተሪያዎቹ ለሌላ  ተግባር መዋላቸው በታዳጊዎቹ ላይ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አሳድሯል" ብላለች።

"ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ብናሳውቅም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም " ያለችው አሰልጣኟ "አሁንም ቢሆን መፍትሄ ይሰጠን" ስትል ጠይቃለች።

በራሳችን ተነሳሽነት ያዘጋጀናቸው ሜዳዎች ሳይቀሩ ለግለሰብ ተሰጥቶብናል፤በተደጋጋሚ ጊዜ ሜዳው እንዲለቀቅ ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም ያለው ደግሞ የታዳጊ ፕሮጀክት አሰልጣኝ ፈይሰል መሀመድ ነው።

"በከተማው የሚገኙ የስፖርት ፕሮጀክቶችን በሙሉ  በአንድ ሜዳ ላይ በተራ ለማሰልጠን በመገደዳችን የምናሰለጥናቸው ታዳጊ ወጣቶች ቁጥር ከእለት ወደ ዕለት እየቀነሰብን ነው" ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

አሰልጣኝ ፈይሰል እንዳለው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በከተማ የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ  ሜዳዎች ለታለመላቸው ዓላማ ሊውሉ ይገባል።

በታዳጊ ፕሮጀክት በእግር ኳስ ከሚሰለጥኑ መካከል ታዳጊ ፋሲል አስፋውና ታዳጊ አረፋት አንዋር እንዳሉት የስፖርት ትጥቅና ሌሎች ግብዓቶች ቢሟሉላቸውም በአሁኑ ወቅት የስፖርት ሜዳዎቹ  ለሌላ አገልግሎት በመዋላቸው ስልጠና ለመውሰድ መቸገራቸውን  ጠቅሰዋል።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር  አቶ ያሲን ዩሱፍ ለቅሬታው በሰጡት ምላሽ  የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎቹ ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ መደረጉን አረጋግጠዋል።

ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ሁሉንም የስፖርት ሜዳዎች ወደ ቀድሞ የስፖርት ማዘውተሪያነት  ተመልሰው የሚፈለግባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል  እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም