በአፋር ክልል የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው

ግንቦት 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ከነገ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

እድሜያቸው ከ6 ወር እስከ 23 ወር የሚሆናቸው ከ200 ሺህ በላይ ሕጻናት ክትባቱን እንደሚወስዱ ገልጿል።

የአፋር ክልል የጤና ቢሮ የእናቶችና ሕጻናት ክትባት ዳይሬክተር አቶ አወል ጉደሌ አሸባሪው ሕወሓት በክልሉ በፈጸመው ወረራ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ሰዎች በተለያዩ መጠለያ ጣቢዎች መሰባሰባቸውንና የሕጻናት ክትባት ስራዉ በመስተጓጎሉ ለበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች መኖራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በሽታውን ቀድሞ መከላከልን ታሳቢ በማድረግ ከግንቦት 10 እስከ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች እድሜያቸው ከ6 ወር እስከ 23 ወር የሚሆናቸው ከ200 ሺህ በላይ ሕጻናት የኩፍኝ ክትባት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ክትባቱ በጤና ተቋማትና በተመረጡ ቦታዎች እንደሚሰጥና የክልሉ አመራሮች፣የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ መሪዎች ለክትባት ዘመቻው ውጤታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ኩፍኝ ሚዝል በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ነዉ።

በሽታዉ በወቅቱ ካልታከመም የአይን ብርሃን ማጣት ፣ለሳንባ ምች፣ ለአንጎል እብጠትና ተያያዥ ኢንፌክሽን ያጋልጣል።

በሽታው በየትኛዉም እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የሚያጠቃ ቢሆንም በተለይም ሕጻናት በተለየ ሁኔታ ያጠቃል።

የጤና ባለሙያዎች የበሽታው መከላከያ ክትባት እንደሆነና ወላጆች ልጆቻቸውን በተገቢው ዕድሜ የመከላከያ ክትባት ተከታትለው እንዲያስከትቡ ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም