“አንድ ሆነን አንድ እንበል” በሚል የአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
“አንድ ሆነን አንድ እንበል” በሚል የአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ ጶግሜ 3/2010 “አንድ ሆነን አንድ እንበል” በሚል መሪ ሀሳብ የአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር እየተከበረ ነው። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተዘጋጀና የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች የተሳተፉበት የዋዜማ ዝግጅት ላይም በርካቶች ታድመውበታል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አለመረጋጋት ሰፍኖ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ሁኔታዎች እየተለወጡና ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ መምጣቱን አውስተው፤ አገሪቷ የቱሪስት መስህቦች፣ ብርቅዬና ተወዳጅ ባህል ያላት በመሆኑ “መጥታችሁ ጎብኙ ተደሰቱ” በማለት ለጎብኚዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር በባህል በኢኮኖሚ ለጋራ ጥቅም በጋራ መስራት እንደምትፈልግም ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው መንግስት ለባህል ዲፕሎማሲ ትኩረት መስጠቱንና ኢትዮጵያ በዓለም ድንቅ መስህቦች ያላት በመሆኑ ለዚሁ ትኩረት እንደምትሰጥ ተናግረዋል። “ቱሪዝም ቀዳሚ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆኑ በመስህቦቻችን እየተደሰታችሁ ለጋራ ጥቅም በጋራ እንስራ” ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል። ከሱዳን የመጡ የባህል ቡድኖችም የዝግጅቱ አካል ናቸው። የኢትዮጵያ የ13ኛ ወር ጳጉሜን በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።