ቀጥታ፡

"ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጉዳይ የቅርብ ተመልካች ሆና አትቀጥልም፤ በቀጣናው የወደብ አማራጮችን ለማስፋት በትኩረት እየሰራች ነው"

ግንቦት 8/2014 /ኢዜአ/ "ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጉዳይ የቅርብ ተመልካች ሆና አትቀጥልም፤ በቀጣናው የወደብ አማራጮችን ለማስፋት በትኩረት እየሰራች ነው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የስራ ክንውን ዛሬ ሲገመግም ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው።

ይህ ትልቅ አገርና ህዝብ የወደብ አማራጭ እንዲኖረው ለማስቻል በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር የጂኦ-ፖለቲካ ስትራቴጂ ተቀርጾ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በኬኒያ፣ በሶማሌላንድ፣ በኤርትራ በመተማመን ላይ የተመሰረተ የወደብ አማራጮችን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ካለት ቅርበት አንጻር በቀጣናው ተጠቃሚ እንጂ የቅርብ ተመልካች ሆና የምትቀጥልበት አግባብ እንደማይኖር አረጋገጠዋል።

በቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያን ያላሳተፈ አደረጃጀት ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሰላማዊ በሆነ መልኩ በትብብር፣ በፍትሃዊነት እና በሚዛናዊነት በቀጣናው ያላትን ጥቅም ማስከበርን ብሔራዊ አጀንዳ አድርጋ መስራቷን ትቀጥላለች  ነው ያሉት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ በዓለም ዓውድ ተደራሽነቷን ለማስፋት አዋጭ ያልሆኑ ኤምባሲዎችን የማጠፍና አዳዲስ ኤምባሲዎችን መከፈት መጀመሯን ጠቅሰው፤ በፓኪስታንና በብሩንዲ ኤምባሲ መክፈቱን  ለአብነት አንስተዋል።

በሰው ኃይል ልማት ረገድ በምዝና ላይ የተመሰረተ ስምሪትና አቅም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ በመማር ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል ብለዋል።

''የሪፎርም ስራው ተስፋ ሰጭ ነው'' ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ምክንያትና ተወዳዳሪነት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማት ምደባ እንዲኖር የሚያስችል ደንብና ስርዓት ተቀርጾ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

የአምባሳደሮች ምደባም አገልግሎትንና ምዘንና መሰረት በማድረግ አገርን ጥቅም ለማስከበር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ የጦር ጀነራሎች እና በአገልግሎት ላይ የቆዩ ሰዎች የአምባሳደርነት ምድባ የሚፈለገውን የዲፕሎማሲ ተልዕኮና በዘርፉ ያላችውን ልምድ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ተደማጭነትና ተዕጽኖ ፈጣሪነትን ከፍ ለማድረግ ውስጣዊ አንድነት፣ ሰላምና ኢኮኖሚን መገንባት የሁሉም ነገር የጀርባ አጥንት መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም