ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በሐምሌ ወር መጨረሻ ሃይል ማስተላለፍ ይጀምራል

ግንቦት 9/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል እየተዘረጋ ያለው የኤሌክትሪክ መስመር በሐምሌ ወር መጨረሻ ሃይል ማስተላለፍ እንዲጀምር ስምምነት ላይ መደረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጻም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም በተለይም ከአጎራባች አገሮች ጋር ያለውን የልማት ትስስርና ግብይት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት አሁንም በመልካም ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የሁለቱ ሀገሮች የድንበር አካባቢ ፀጥታ፣ የመሰረተ ልማት ትስስር እንዲሁም የንግድና የኢኮኖሚ  ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች ተደርገው በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተመረጡ የትኩረት መስኮች ላይ መተባበር  የሚያስችል ልዩ ስምምነት መደረጉንም አስታውሰዋል።

ለኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ምርቶች በአማራጭነት ያገልግላል ተብሎ የሚታሰበው የኬንያው ላሙ ወደብ ፕሮጀክትም ሁለቱን ሀገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ የመሰረተ ልማት አካል መሆኑንም አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

የገቢና ወጪ ንግድ ልውውጡን በአንድ የጋራ ቁጥጥር ማዕከል ለማስተናገድ የሚያስችል አሰራር በጋራ ተዘርግቶ ስራ መጀመሩንም አስታውሰዋል።

በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚ ለማደረግ የድንበር ንግድ ረቂቅ ስምምነት ተዘጋጅቶ ለውሳኔ መቅረቡንም ጠቁመዋል።

ሁለቱን ሀገራት በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረትም በጥሩ አፈፃፀም ላይ መሆኑን ጠቅሰው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው በሐምሌ ወር መጨረሻ ሃይል ማስተላለፍ ይጀምራል ብለዋል።

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ በሐምሌ 2014 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ሃይል ማስተላለፍ እንዲጀምር ሁለቱ አገሮች ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ሁለቱን ሀገሮች ሊያስተሳስሩና ለቀጣናዊ ትብብርና ለህዝቦች ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሚና ያላቸው የተጀመሩ የጋራ ፕሮጀክቶች ፍጻሜ እንዲያገኙ የቅርብ ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም