ኢትዮጵያዊያን በሺህ ዓመታት ጉዟቸው ያዳበሩትን የተሰናሰለ የጋራ እሴት በማስጠበቅ ለሀገር አንድነት መስራት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን በሺህ ዓመታት ጉዟቸው ያዳበሩትን የተሰናሰለ የጋራ እሴት በማስጠበቅ ለሀገር አንድነት መስራት ይጠበቅባቸዋል
ግንቦት 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በሺህ ዓመታት ጉዟቸው ያዳበሩትን የተሰናሰለ የጋራ እሴት በማስጠበቅ ለሀገር አንድነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አሳሰቡ።
ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩ የመተባበር የመቻቻል እንዲሁም የመከባበር በርካታ ማህበራዊ እሴቶች ባለቤት መሆኗ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እነዚህን ማህበራዊ እሴቶች የሚሸረሽሩ ተግባራት በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታት እነዚህ የዳበሩ ማህበራዊ እሴቶች እንዲጠፉ ብዙ መጥፎ ስራዎች መሰራታቸውን የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ይናገራሉ።
ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ''ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያልተሰራ ስራ የለም'' ብለዋል።
''እኩይ አላማ ያነገቡ አካላት በአንዳንድ አገራት ላይ ያጋጠሙ እልቂት ታሪኮች በኢትዮጵያ ላይ እንዲፈጠሩ የቻሉትን ያህል ቢያደርጉም አልተሳካም" ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን የበርካታ አመታት የአብሮነት እሴት ስላላቸው በአንድነት ቀጥለዋል ነው ያሉት።
በመሆኑም ''እነዚህ ለዘመናት በአብሮነት እንድንቆይ ያደረጉንን እሴቶች ማጎልበት ይገባል'' ሲሉ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ገልጸዋል።
የሀይማኖት አባቶች ልጆቻቸውን የመምከር በተለይም ምክንያታዊነት ያለው ትውልድ በመፍጠር ረገድ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ያሳስባሉ።
ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ትምህርት ቤቶች፣ የእምነት ተቋማት እንዲሁም ቤተሰብ ትውልዱ ላይ መስራት እንደሚገባቸው ጨምረው አሳስበዋል።
እነዚህ ባለድርሻ አካላት በትውልዱ ላይ ካልሰሩ ለትውልድ መፍረስ ቀዳሚ ተወቃሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።