ዲፕሎማሲያዊ ጫናን ለመቋቋም ውስጣዊ አንድነታችንን መጠበቅ አለብን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዲፕሎማሲያዊ ጫናን ለመቋቋም ውስጣዊ አንድነታችንን መጠበቅ አለብን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ
ግንቦት 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዲፕሎማሲያችን ላይ ያለውን ጫና ለመቋቋም ውስጣዊ አንድነታችንን ማጥበቅና መጠበቅ አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስገነዘቡ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያቀረቡ ያሉት አቶ ደመቀ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በተለያየ መንገድ ጫና እየደረሰበት ይገኛል።
እየደረሰ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና በኢትዮጵያ ህዝብ ጽናት፣ በዳያስፖራው ተሳትፎ እና በኢትዮጵያ ወዳጆች ትብብር መቋቋም መቻሉን አመልክተዋል።
ለዚህም አስተዋጽኦ ለመላው ህዝብ፣ ለዳያስፖራውና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በጋራ ርብርቡ ጫናዎች የመለዘብ ምልክት ቢያሳዩም ጫናው በመቀጠሉ በትብብር መስራቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
“የዓለም ስርዓት ተገማች ያለመሆን፤ በተለያዩ ፍላጎቶችና የአሰላለፍ ለውጦች ምክንያት የዲፕሎማሲ ስራችን በእጅጉ ፈተና የበዛበት ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ውስጣዊ አንድነታችንን ማጥበቅና መጠበቅ አለብን ብለዋል።
ሰላምን ከማረጋገጥ ሂደት ጎን ለጎን በማስገንዘብና በማለዘብ ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነትን አጠናክሮ መቀጠል ይጠይቃል ሲሉ ገልጸዋል።
በጂኦ ፖለቲካ ፍላጎትና በልዩ ልዩ ውስጣዊ ሁኔታዎች ዲፕሎማሲው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ቀድሞ መንቀሳቀስ የሚፈለግበት ዘመን ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።