ቀጥታ፡

የደን መራቆት ችግር እየተባባሰ መምጣቱን የኢትዮጵያ የደን ባለሙያዎች ማህበር ገለፀ

አዲስ አበባ  ጶግሜ 3/2010 በኢትዮጵያ ያለው የደን መራቆት ችግር በአሳሳቢ ደረጃ እየተባባሰ መምጣቱን የኢትዮጵያ የደን ባለሙያዎች ማህበር ገለፀ። ችግሩን ለመፍታት መንግስት ከዘርፉ ልማት ጋር በተያያዘ የሚሰሩና ተበታትነው የሚገኙ ተቋማትን አደረጃጀት ማስተካከል ይጠበቅበታል ተብሏል። የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ውባለም ታደሰ እንደሚሉት፤ የደን ዘርፉ ለአገሪቱ ስነ-ምህዳራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታዎች ያሉት ቢሆንም ተገቢው ትኩረት እየተሰጠው አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ በእርሻ መሬት መስፋፋትና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ በየዓመቱ በአማካኝ 92 ሺህ ሄክታር ደን ይጨፈጨፋል፤ በምትኩ የሚተከለው ዛፍ ግን  ከ20 ሺህ ሄክታር አይበልጥም። በአሳሳቢ መጠን እየጠፋ ያለው የደን ኃብት ታዲያ የአገሪቱን የአየር ሁኔታ በማዛባት ለተፈጥሮ አደጋዎች ከማጋለጥ ባሻገር ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳትም እያስከተለ መሆኑን ዶክተር ውባለም ይገልፃሉ። ለደን ኃብት ልማት የተመቸችው አገር ኢትዮጵያ ለተለያዩ የግንባታ ግብአቶች የሚያስፈልጋትን ጣውላና ሌሎች የደን ውጤቶች ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ከውጭ በማስገባት ለኢኮኖሚ ጉዳት መጋለጧን ጠቁመዋል። በደንና በተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ያሉ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመከላከል መንግስት በዘርፉ ልማት ዙሪያ የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጥ ማምጣት የሚጠበቅበት እንደሆነ አመልክተዋል። "አሁን ያለው አደረጃጃት በተዋረድና ወጥነት ባለው መንገድ በክልልች ያልተዘረጋ በመሆኑ መንግስት በዘርፉ ያቀዳቸውን ታላላቅ ግቦች ለማሳካት እንቅፋት ሆኖበታል" ሲሉ ዶክተር ውባለም ገልፀዋል። በመሆኑም በዋነኝነትም ተበታትነው የሚገኙትን የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን፣ የባዮስፌር ሪዘርቭ፣  የተፈጥሮ ሃብትና ጥምር እርሻ ደን፣ የተፈጥሮ ሙጫና እጣን ምርትና ገበያ እንዲሁም የባዮማስ ኢነርጂ መስሪያ ቤቶችን በአንድ ጥላ ሥር ማሰባሰብ ይገባል። እነዚህ ተቋማት የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሥር ቢደራጁ መልካም መሆኑንም ጠቁመዋል። አደረጃጀቱም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍና የአካባቢ ጥበቃ ስራን በተገቢው መንገድ ለመምራት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉም ተናግረዋል። "ሆርን ኦፍ አፍሪካ" በሚል ስያሜ የሚጠራ ተቋም የደን ተመራማሪና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር አዘነ በቀለ ውሃን መሰረት ያደረገ የኃይል አቅርቦትን በዘላቂነት ማሳደግ ግቡ ያደረገውን የአገሪቱን የልማት አቅጣጫ ለማሳካት የደን ዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም ግን በቅርብ ጊዜ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት በጣና ሐይቅ ብቻ በዓመት እስከ ስድስት ሚሊዮን ቶን የአፈር ደለለ ወደ ሃይቁ እንደሚገባ መረጋገጡን ተናግረዋል። "በዚህም የተነሳ የውሃ ሃብታችን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ከመሆኑም በላይ ግድቦች፣ ሃይቆችና ወንዞች በደለል በመሞላት መስጠት የሚገባቸውን ግልጋሎት እንዳይሰጡም እንቅፋት በመሆን ላይ ናቸው" ብለዋል። በመሆኑም መንግስት በአሁኑ ጊዜ እያካሄደ ባለው የተቋማት አደረጃጀት ማሻሻያ ተግባር ላይ ለደን ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም