የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢነርጂ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢነርጂ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አጸደቀ
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢነርጂ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ ትናንት አጸደቀ። አዋጁ የብሔራዊ ዋና ዋና መስመሮች የኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፍና የማሰራጨት ሥራ ለመንግስት ብቻ የተከለለ መሆኑ ተደንግጓል። የምክር ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር አማረ እንደገለጹት፤ አገሪቷ በአሁኑ ወቅት ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጊዜያት ውስጥ ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር ቁልፍ ግብዓት ከሆኑ መካከል ደግሞ ኢነርጂ በተለይም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ዋነኛውና አንዱ መሆኑ ተጠቁሟል። በመሆኑም አዋጁ የግሉ ዘርፍ በዚህ መስክ በበቂ ሁኔታ እንዲሳተፍ፣ የህግ ማዕቀፉን ምቹና ሳቢ ለማድረግ እንዲሁም ማንኛውም የተፈቀደለት ህጉንና አሰራሩን ጠብቆ በዘርፉ ተሳታፊ እንዲሆን ያለመ ነው። በተጨማሪም የልማት ስራው የሚወስደውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገና የተቀናጀ አሠራር መዘርጋት አስፋላጊ መሆኖ ስለታመነበት ነው ሲሉ አብራርተዋል። በዚህም በቀድሞ አዋጅ የነበረው ለኢነርጂ ልማቱ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ታሳቢ ያላደረገ በመሆኑ የአገሪቷን ልማት ለማሳለጥና በዚህ በኩል ያለውን ማነቆ መፍታት አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊነቱ እንደታመነበት ተገልጿል። ምክር ቤቱም የአዋጁን ማብራሪያና የውሳኔ ሃሳብ ካዳመጠ በኋላ አዋጅ ቁጥር 1085/2010 በማድረግ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።