በአዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ አገሮች አምባሳደሮች የእንኳን አደረሳቸሁ ስጦታ ተበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ አገሮች አምባሳደሮች የእንኳን አደረሳቸሁ ስጦታ ተበረከተ
አዲስ አበባ ጶግሜ 3/2010 የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ አገሮች አምባሳደሮች የእንኳን አደረሳችሁ ስጦታ አበረከተ። ሚኒስቴሩ "አበባይሆሽ"ን በሚጫወቱ ልጃገረዶች ታጅቦ በየኤምባሲዎቹ መኖሪያ በማቅናት ለአምባሳደሮቹ ያበረከተው የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች አልባሳትን ነው። በመስሪያቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከወነው ይህ የእንኳን አደረሳችሁ ጉብኝትና ስጦታ ዓላማ የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በዓል ባህላዊ እሴት ለዓለም ለማስተዋወቅና በአዲስ አበባ የሚኖረው ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆን ለማድረግ እንደሆነ ተጠቁሟል። የሚኒስቴሩ ህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ካሳሁን አያሌው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የ'እንኳን አደረሳቸሁ' ስጦታ የተበረከተው መቀመጫቸው በአዲስ አበባ ለሆኑ ሰባት አምባሳደሮች ነው። ከተቀረው ዓለም ሁሉ በልዩ ሁኔታ የዘመን መለወጫ በዓል በሚከበርባት ኢትዮጵያ በመገኘታቸው የተለየ ስሜት እንደሚፈጥርባቸው በተለይ በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር ኤልማን አብዱላየቭ ተናግረዋል። በመጪዎቹ ዓመታት ግን ሁሉንም አምባሳደሮች በዚህ መልኩ ለመጎብኘትና የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግና ታሪክ የማስተዋወቅ ሰፊ ተግባራት ለማከናወን መታቀዱ ተጠቅሷል።