የሞጆ - ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታ የመንገድ ዘርፉ የደረሰበትን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ደረጃ ያሳያል

ግንቦት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሞጆ - ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታ የመንገድ ዘርፉ የደረሰበትን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ደረጃ እንድናውቅ አድርጎናል ሲሉ ፕሮጀክቱን የጎበኙ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለሙያዎች ገለጹ።

የሞጆ - ሃዋሳ ፈጣን የመንገድ ፕሮጀክት አካል የሆነው ክፍል አራት የአርሲ ነጌሌ - ሃዋሳ 52 ኪ.ሜ የአስፋልት ግንባታ ፕሮጀከት በአስተዳደሩ ሠራተኞች ተጎብኝቷል።

የአርሲ ነጌሌ - ሃዋሳ የመንገድ ፕሮጀከት የሚገነባው በዓለም አቀፉ የሥራ ተቋራጭ ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ነው።   

የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ቤጂንግ ኤክስፕረስ ዌይ ሱፐር ቪዥን ካምፓኒ ከውሃን ጄ አይ ኦኬ ኢንጅነሪንግ ኮንሰልታንሲ ጋር በጋራ በመሆን እየሰሩት ነው።

መንገዱን ለመገንባት የሚውለው ወጪ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን ወጪው 85 በመቶ በቻይናው ኤግዚም ባንክ ሲጨፈን ቀሪው 15 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው።

በአርሲ ነጌሌ - ሃዋሳ የመንገድ ፕሮጀክት የአፈር ቆረጣና ድልዳሎ ሥራ፣ የአፈር ሙሌት፣ የስትራክቸር ሥራዎች፣ የሰብ ቤዝ ሥራ፣ የውሀ ማፋሰሻ ቱቦዎች ቀበራ፣ የድልድይ ግንባታ፣ የጠጠር ንጣፍ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

ፕሮጀክቱን የጎበኙት የተቋሙ የምህንድስና ባለሙያዎች፤ የሞጆ - ሃዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታ የመንገድ ዘርፉ የደረሰበትን ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ደረጃ እንድናውቅ አድርጎናል ብለዋል።

ይህንንም የዘርፉን ቴክኖሎጂ በመቅሰም ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶችን በተሻለ ጥራት ለመገንባትና ለኅብረተሰቡ ደረጃዎን የጠበቀ የመንገድ አገልግሎት ለመሥጠት እንደሚጥሩ ጠቁመዋል።   

ከጎብኚዎቹ መካከል፤ ኢንጅነር ደፋሩ ደረሰ፤ እስካሁን ካያቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ የተለየ ልምድ ያገኘበት መሆኑን ገልጿል።

በተለይም የመሬት መሰንጠቅን ለመከላከል ጥቅም ላይ የዋለው ቴክኖሎጂ የተለየና አዲስ እውቀት ያገኘበት መሆኑን ተናግሯል።

ለግንባታ ምቹ ያልሆኑ መልክአ ምድሮችን ምቹ በማድረግ እንዴት መገንባት እንደሚቻል የተሻለ እውቀት አግኝቻለሁ ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ኢንጅነር ተመስገን አምላክ በበኩሉ ለምህንድስና ፈታኝ የሆኑ መልክአ ምድሮች እንዴት ምቹ ማድረግ እንደሚቻል ማየቱን ገልጿል።

ምንም እንኳን ስለ ቴክኖሎጂው በትምህርት ቢሰጥም እንዴት ተግባራዊ እንደሚደረግ በነበረው ቆይታ መመልከቱን ተናግሯል።

የመሬት መደርመስን ለመከላከል ጥቅም ላይ የዋሉት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አዲስ እውቀት አግኝቼበታለሁ ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ኢንጅነር ሃያት አለማ ናት።

ቴክኖሎጂው በመንገድ ግንባታ ዘርፍ እስካሁን ካየቻቸው ፕሮጀክቶች የተለየ ስለመሆኑም ገልጻለች።

በጉብኝቱ ለቀጣይ ሥራዎች ግብዓት እንዳገኘችበትም ተናግራለች።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የትራንስ አፍሪካ አህጉር አቋራጭ 10 ሺህ ኪሎሜትር የፍጥነት መንገድ አካል የሆኑትን የሞጆ መቂና የመቂ ባቱ መንገዶችን ማስመረቃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም