ቀጥታ፡

የዓለም ባንክ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር የ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ

ግንቦት 8 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ለማድረግ የዓለም ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስቴር የ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።

የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ጋር ተፈራርመዋል።

የድጋፉ ዓላማም በአማራ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በጦርነትና ግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ዜጎችን ለማቋቋም ያለመ ነው።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን፤ የዓለም ባንክ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድህነትና ዘላቂ ልማት ጎን እንደሚቆም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ጦርነትና ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲቀጠፍ የሰብአዊ ጉዳቱና የንብረት ውድመትም በስፋት ተከስቷል።

በዚህም መልከ ብዙ ማህበራዊ ምስቅልቅል እና አለመረጋጋት መከሰቱን አስታውሰው መልሶ ለመገንባት የሁሉንም ድጋፍና ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በጦርነቱ የተፈናቀሉትን ጨምሮ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማገዝ የዓለም ባንክ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ በበኩላቸው ከዓለም ባንክ ጋር የተፈረመው የድጋፍ ስምምነት በጦርነትና ግጭት ተጎጂ የሆኑ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የጤና፣ የትምህርትና የንጹህ መጠጥ ውሃ መሰረት ልማት ዝርጋታ ብሎም በፆታዊ ጥቃት ተጎጂ የነበሩ ሴቶችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም ይውላል ብለዋል።

የዓለም ባንክ የድጋፍ ስምምነት በጦርነቱ ከደረሰው ውድመት አንፃር ብዙ ባይሆንም የተጎዱ አካባቢዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

በጦርነት፣ በድርቅ እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተደራራቢ ጉዳት ሰለባ የሆነውን ኢኮኖሚ ለማገዝ እና የጉዳት ሰላባ የሆኑ ወገኖችን ለመደገፍ የድጋፍ ስምምነቱ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የልማት አጋር በመሆን ለሚያደርገው ድጋፍ ያመሰገኑት ሚኒስትሩ ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችም ገቢራዊነት በአጋዥነቱ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በተያዘው ዓመት 5 ቢሊዮን ብር መመደቡን አስታውሰው በ2015 በጀት ዓመት 20 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም