የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር አስችሏል
አዳማ፤ ግንቦት 08 ቀን 2014 (አዜአ) “በበልግ ወቅት የነበረው የአየር ጠባይ ትንበያ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ድርቅ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንድንቋቋመው አስችሎናል” ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢታፋ ገለፁ።
የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ ግምገማና የመጪው የክረምት ወቀት የአየር ጠባይ ትንበያ ይፋ የሚደረግበት መድረክ ዛሬ በአዳማ በመካሄድ ላይ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢታፋ በመክፈቻው ላይ እንደገለፁት የበልግ ወቅት የአየር ሁኔታ ትንበያ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ድርቅ በዜጎች ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ቀድመን እንድንዘጋጅበት አድርጎናል ብለዋል።
በዚህም ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመቋቋም አቅም እንዲንገነባ ከማስቻሉም ባለፈ ሊደርስ የነበረውን አደጋ ማስቀረት እንዲንችል አግዞናል ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የነበረው ድርቅ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ጫና ማሳደሩን የገለፁት ሚኒስትሩ ወቅታዊና ትክክለኛ የአየር ጠባይ ትንበያ ለህብረተሰቡ በማድረስ ረገድ አበረታች ውጤት መኖሩንም ተናግረዋል።
በቀጣይ ክረምት አርሶ አደሩ ሊኖር የሚችለውን የዝናብ ስርጭት ተከትሎ በአግባቡ እንዲጠቀም ለማድረግ ትክክለኛና ጥራት ያለውን ትንበያ ተደራሽ ማድረግ ላይ አሁንም ይበልጥ በትኩረት የምንሰራበት ጉዳይ ነው ብለዋል።
አርሶ አደሩ የክረምት የዝናብ ስርጭት ሁኔታን ተገንዝቦ በወቅቱ የግብርና ልማቱን ማከናወን እንዲችል አሁንም ወቅታዊና ጥራት ያለው የአየር ጠባይ ትንበያ በተገቢው መንገድ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሴክተሮች ለይተን በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።
ዘመናዊ የሚትሮሎዎጂ ቴክኖሎጂን ተጠቅመን በበልግ ወቅት የሚኖረውን የዝናብ ስርጭትና ሊፈጠሩ የሚችሉ ተፅዕኖዎች ላይ መሰረት ያደረገ የአየር ትንበያ ለተጠቃሚዎች ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
በተለይ በመጪው ክረምት ትክክለኛ የአየር ንብረት ትንበያና መረጃ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ዘንድ እንደርስና የታሰበው ውጤት እንዲመጣ እየሰራን ነው ብለዋል።