በክልሉ እየቀነሰ የመጣውን የክትባት ሽፋን ለማሳደግ እየተሠራ ነው - ጤና ቢሮ

አሶሳ፤ ግንቦት 07 / 2014 (ኢዜአ)፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በፀጥታ ችግር ምክንያት እየቀነሰ የመጣውን የህጻናት ክትባት ሽፋን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ጤና ቢሮ የህጻናት ክትባት ሽፋን በሚያድግበት ጉዳይ ላይ  ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ  በአሶሳ ከተማ  ውይይት አካሂዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ አብዱረሂም በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች አጋጥሞ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የህጻናት ክትባት ሽፋን መቀነሱን አመልክተዋል።

በክልሉ በካማሺ ዞን የህጻናት ክትባት ሽፋን አምስት በመቶ ላይና  በመተከል ዞን ደግሞ 43 በመቶ ላይ መሆኑን በማሳያነት ተናግረዋል።

ይህም ከአንድ ዓመት በፊት ከ90 በመቶ በላይ የነበረው የክልሉን የሕጻናት የክትባት ሽፋን አሁን ወደ 60 በመቶ ዝቅ ማድረጉን ተናግረዋል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የክፉኝ በሽታ በወረርሽን መልክ መከሰቱን ገልጸው፤ ህጻናት በብዛት ወደ ጤና ተቋማት እንዲመጡ በመቀስቀስ ክትባት እንዲወስዱ በማድረግ የክልሉን ክትባት ሽፋን  ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ክትባት ሳምንት ምክንያት በማድረግ ከግንቦት 10 እስከ 17 ቀን 2014 ዓ.ም በክልሉ የሚገኙ እድሜአቸው አምስት ዓመትና በታች የሆናቸው ህጻናት የክፉኝ ክትባት እንደሚወስዱ አስታውቀዋል፡፡

በዘመቻው የአንጀት ጥገኛ ትላትልን ጨምሮ የተለያዩ መድሃኒቶች በነፃ የሚቀርቡ ሲሆን፤ የምግብ እጥረት ያለባቸው ህጻናትን የመለየት ስራም ይካሄዳል ብለዋል።

የበየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ክትባት በወረርሽኝ መልክ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ያለውን ፋይዳ በመረዳት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የወረዳ ጤና ጽዕፈት ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስራዎች ላይ ጫና እየፈጠረ የሚገኘው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት መፍትሄ እንዲፈለግለት ጠይቀዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው ፊሊጶስ በክልሉ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት መንስኤ በመንግሥት መዋቅርና በንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አካላት የግል ጥቅማቸውን በማስቀደማቸው የፈጠሩት ችግር እንደሆነ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ችግሩን  ለመፍታት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም