የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል አለበት

199

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ጋር የተለያዩ የጸጥታ ሥራዎች ሲሰራ ቆይቷል።

በተለይም ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ከኅብረተሰቡ ጋር ባካሄደው ተግባራት የተለያዩ አጀንዳ ያነገቡ አካላት የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ ያደረጉትን ጥረት ለማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።

ለአብነትም በመዲናዋ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ድምጽ አልባ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ሕገ-ወጥ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ገንዘቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉንም ነው የገለጹት።

ለዚህም ኅብረተሰቡ ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ የአካባቢው ሰላምን ለማስጠበቅ ከጸጥታ አካላቱ ጋር ያደረገው ዘርፈ-ብዙ ትብብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ሠላምና ፀጥታ አስተማማኝ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ጸጥታን የሚያደፈርሱ የተለያዩ ጉዳዮችን በንቃት እንዲከታተልም ጥሪ አቅርበዋል።

በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ኅብረተሰቡን ለማሸበር ከሚነዙ የተለያዩ መረጃዎች ኅብረተሰቡ እራሱን እንዲጠብቅም ተናግረዋል።

የመዲናዋ ፖሊስ የከተማዋን ሠላም ለማስጠበቅ ከኅብረተሰቡ ጋር ከሚያደርገው ትብብር ጎን ለጎን ከአጎራባች ክልሎችም ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መዲናዋን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ አጀንዳ ያነገቡ አካላትን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም ሰፊ እድል እንደፈጠረለትም ነው ምክትል ኮማንደሩ ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም