በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ367 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ367 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
ድሬዳዋ፤ ግንቦት 6/2014(ኢዜአ) በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ወደ ውጭ ከተላኩ የግብርና ምርቶች ከ367 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የድሬዳዋ ውጭ ንግድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ገቢው ከእቅዱ በ7 ነጥብ 5 በመቶ ፤ከአምናው ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ11 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሐድጎ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የተገኘው ገቢ ከሐምሌ 1 ቀን 2013 እስከ ሚያዝያ 30/2014 ዓ.ም. ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት ከተላኩት የግብርና ምርቶች ነው፡፡
ገቢው በዋናነት የተገኘው ከጫት፣ ከቡና፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ፣ ከቁም እንስሳት፣ ከቅመማ ቅመምና ከጌጣጌጦች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሶማሊያ፣ ሶማሌላንድ፣ ጅቡቲ፣ አውሮፓ ሀገራትና አሜሪካ ምርቶቹ የተላኩባቸው ሀገራት መሆናቸውን አስረድተዋል።
የተገኘው ገቢ ከእቅዱ ሆነ ከአምናው ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው የገለጹት ኃላፊው፤ በዋናነት በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ማስተካከያ በመደረጉ ለገቢው መጨመር በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
ከግብርና ምርቶች የሚገኘውን ገቢ በእጥፍ ለማሳደግ በውጭ ሀገራት ያላቸው ተቀባይነት ለመጨመር በምርቶቹ ደረጃና ጥራት ላይ የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
በተለይ የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ከፍተኛ የቁም እንስሳት ሃብትን ጥቅም ላይ ለማዋል ባለፉት ዓመታት ተሰርተው በነበሩ የተቀናጁ ተግባራት በዓመት እስከ ዘጠና ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ ግን በዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም ምክንያቱ በዘርፉ የሚካሄደው የኮንትሮባንድ ንግድ መባባስ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የፀጥታ አካላትና የፌዴራል ፖሊስ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የጀመሩትን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው ነው አቶ ተስፋዬ ያሳሰቡት፡፡
በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በኮንትሮባንድ ሊወጡ የነበሩ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የግብርና ምርቶች በቁጥጥር ሥር መዋሉን ጠቁመዋል፡፡
በድሬዳዋ የኢንዱስትሪ መንደር ሥራ ላይ የተሰማሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ ዮሐንስ አበበ በሰጡት አስተያየት፤ ከግብርና ምርቶች የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ልክ እንደ አበባ ምርት በጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይ ድሬዳዋ በዘመናዊ ባቡርና በኮንክሪት አስፓልት መንገድ ከጅቡቲ ወደብ የተያያዘ መሆኑ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ "ኦርጋኒክ" ምርት ለገበያ ማቅረብ ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ቡናም ደረጃውን ባሟላ ሁኔታ ተቆልቶ፣ ተፈጭቶና አሽጎ መላክ የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረው፤ ለዚህ ሥራ ደግሞ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ናሙናዊ ሥራዎችን ከገበሬው እርሻ ጀምሮ ውጭ እስከ መላክ ድረስ ያለውን በሠርቶ ማሳያ ማስተማር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡