ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለአብርሃ ባህታ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ድርጅት ድጋፍ አደረገ

121

ሐረር ፤ ግንቦት 5/2014(ኢዜአ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለአብርሃ ባህታ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ድርጅት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ዊልቸሮችና ሌሎች ለአካል ድጋፍ የሚያገለግሉ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ ፕሮፌሰር ጀይላን ወልይ በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ፤ ሀገራቸውን በተለያየ መልኩ ሲረዱና ሲያግዙ የነበሩ አረጋውያንን ችግር ለማቃለል እንዲያግዝ ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን ማድረጉን ተናግረዋል።

''ዩኒቨርሲቲው ሁሌም ማህበረሰብ ተኮር ስራዎችን በትኩረት ያከናውናል'' ያሉት ፕሮፌሰር ጀይላን፤ በተለይ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለችግር ለተጋለጡት ወገኖች ድጋፉን  አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

የሐረሪ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ምስራቅ እሸቴ፤  ድርጅቱ ለበርካታ ዓመታት ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ አረጋውያንን በመያዝ በተቀዛቀዘ መልኩ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን  ጽህፈት ቤቱ ከመቆዶኒያ የአረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ተቋም ጋር በፈጠረው ግንኙነት  112 አረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ  እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያበረከተው  ድጋፍ ለአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲልም የፍራሽና አልጋ ድጋፍ እንዳደረገም ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን የገለጹት በድርጅቱ የመቆዶኒያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ  አቶ ዳንኤል መኩሪያ ናቸው።

አረጋውያኑና አካል ጉዳተኞች ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የአካል ድጋፉ የተለገሳቸው አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችም  ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

የአብርሃ ባህታ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ  ድርጅት በትውልደ ኤርትራዊ  በሆኑት አብርሃ ባህታ በ1958 መቋቋሙን  መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም