የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዜጎችን ከበደል የሚከላከልና አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ ምክር ቤቱ አሳሰበ

67

አዲስ አበባ ግንቦት 5/2014 /ኢዜአ/ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዜጎችን ከበደል የሚከላከልና አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የሕግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል።

ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፤ተቋሙ የአስተዳደር በደልን በመከላከልና አቤቱታዎችን መርምሮ እልባት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል።

አስተዳደራዊ በደልን ለመከላከል በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ በመደበኛ፣ በድጋሚ ቁጥጥርና በጥናት ፍተሻ መደረጉንና የተገኙ ችግሮች እንዲቀረፉ መመሪያ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በአዲስ አበባ የኮንዶሚኒየም ቤት ማስተላለፍ ላይ ያሉ አስተዳደራዊ በደሎች መፈተሻቸውን፣  በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሂደት ላይ ዳሰሳዊ ቁጥጥር መደረጉን አንስተዋል።

በተለያዩ ከተሞች የመሬት ልማትና አጠቃቀም እንዲሁም የፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ምን እንደሚመስል ፍተሻ መደረጉንም እንዲሁ፡፡

ተቋሙ ልዩ ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች እያገኙ ያሉትን አገልግሎት ዳሰሳ ያደረገ ሲሆን፤ በፖሊሲዎች፣ በሕግና መመሪያዎች የተቀመጡ መስፈርቶች በሚፈለገው ልክ እየተተገበሩ እንዳልሆነ አረጋግጠናል ነው ያሉት።

በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ድርቅ ዙሪያ በተደረገው ዳሰሳዊ ቁጥጥርም የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ስርዓት በአግባቡ ባለመተግበሩ በእንስሳት ሀብት ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

ሌላው የዜጎችን በደል እያከበደው የመጣው የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ መናር ጉዳይ ነው ያሉት ዋና እንባ ጠባቂው፤ በተለይም የሸቀጦች ዋጋ  በደላሎች የሚወሰን መሆኑ ሁኔታውን የከፋ አድርጎታል ብለዋል።

በአጠቃላይ ለተቋሙ ከቀረቡ አቤቱታዎች መካከል በቅድመ-ምርመራ 141 መዝገቦች መፍትሔ ሲሰጣቸው 196 ደግሞ በውይይት  መፈታታቸውን ጠቅሰዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ኅብረተሰቡ በአስተዳደራዊ በደሎች እየተማረረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ተቋሙ ከቁጥጥር ሥራ በተጨማሪ ዜጎችን ያማረሩ በደሎች ምላሽ እንዲያገኙ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት ነው ያሉት፡፡

ዋና እምባ ጠባቂው ዶክተር እንዳለ በሰጡት ምላሽ ተቋሙ በህዝብ ላይ በደል የሚያደርሱ ተቋማትን በተመለከተ እርምጃ እንዲወሰድ ለፍትህ ተቋማት፣ ለመገናኛ ብዙኃንና ለምክር ቤቱ ሪፖርት ማቅረቡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ በቀጣይ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ተከታትሎ በመሥራት ረገድ ያለበትን ክፍተት ለማስተካከል እንደሚሰራም  አረጋግጠዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዕጸገነት መንግስቱ ተቋሙ የህዝብን በደል ለመከላከልና በየተቋማቱ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

በተቋማት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት አርዓያነት ያለው ተግባር ሊያከናውን እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የዜጎችን እምባ የሚያብስ ጠንካራ ተቋም መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡

ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም