በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በአገሪቱ ምዕራብና የደቡብ ምዕራብ ተፋሰሶች ላይ የተሻለ ዝናብ ይኖራል

150

ግንቦት 5/2014(ኢዜአ) በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በአገሪቱ ምዕራብና የደቡብ ምዕራብ ተፋሰሶች ላይ የተሻለ የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የበልግ ዝናብ በአገሪቱ የምዕራብ አጋማሽ  አካባቢዎች እየተስፋፋ ይሄዳል።

እነዚሁ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚያገኙም የሚቲዎሮሎጂ ትንበያዎች ያመለክታሉ ነው ያለው።

የዝናቡ ሁኔታ በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ ከሞላ ጎደል ቀጣይነት እንደሚኖረውም አመልክቷል።

በእነዚሁ ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች ቀጣይነት እንደሚኖራቸውም እንዲሁ።

ይህም በተለያየ የዕድገት ደረጃዎች ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት እንደሚረዳም ጠቁሟል።

በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም እንዲሁ።

በተጨማሪም ለመኸር ግብርና ዝግጅት መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥርም ኢንስቲትዩቱ በላካው መግለጫ አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም