ሊጉ በፓርቲው ጉባኤ ለተቀመጡ አቅጣጫዎች ተፈፃሚነት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አስታወቀ

71

አዳማ ፤ ግንቦት 05/2014.(ኢዜአ) በብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለተቀመጡ አቅጣጫዎች ተፈፃሚነት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የፓርቲው የወጣቶች ሊግ አስታወቀ።

የሊጉ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በፓርቲው ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ዙሪያ በአዳማ ከተማ እየመከረ ነው።

በምክክር መድረኩ የሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ እንዳለው፤ በጉባኤው የዜጎችን አጠቃላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት አቅጣጫዎች ተቀምጧል።

ሊጉም እየመከረ ያለውም ጉባኤውን ተከትሎ ባለፉት ወራት በየደረጃው ካሉ አባላቱ ጋር ባካሄዳቸው የውይይት መድረኮች ከወጣቶች በተነሱ አበይት ጉዳዮች ላይ መሆኑን  ገልጿል።

የምክክር መድረኩ ዓላማ በፓርቲው ጉባኤ የተቀመጡ ቁልፍ አቅጣጫዎች  በየደረጃው የሚገኙ የሊጉ አባላት ግልፅ ግንዛቤ አግኝተው ለተፈፃሚነቱ ርብርብ እንዲያደርጉ ለማስቻል መሆኑን ተናግሯል።

ሊጉ በጉባኤው ትኩረት በተሰጣቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለአንድ ወር በ750 ከተሞችና ከ8 ሺህ 200 በላይ በሚሆኑ ቀበሌዎች ላይ ከወጣቶች ጋር ሰፊ ውይይት መካሄዱንም ወጣት አክሊሉ ጠቅሷል።

እንደ ወጣት አክሊሉ ገለጻ፤  መላው የሊጉ አባላት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች፣ የወጣቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት በሚፈቱበት አግባብ ሰፊና ጥልቅ ውይይት አድርገዋል።

የከተማ ግብርና ንቅናቄ፣ ወጣቱን እየፈተኑ ያሉ የመልካም አስተዳደር ማነቆዎች፣ የሰላም እጦትና የስራ አጥነት ችግሮች የውይይቶቹ አበይት አጀንዳዎች ናቸው ብለዋል።

ወጣቶችን ጨምሮ ሌሎችንም ዜጎችን የልማት፣ የሰላም፣ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ መንግሥትና ፓርቲው ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች ማስቀመጣቸውን ተመልክቷል።

እነዚህን አቅጣጫዎችና የማስፈፀሚያ ስልቶች እንዲሳኩ የሊጉ አባላትና አመራሮች ከመንግሥትና ከፓርቲው ጎን ሆነው የድርሻቸውን እየተወጡ ነው ብሏል።

በዚህም ወጣቶች  ፀረ ሰላም ቡድኖችን  ከማጋለጥ ጀምሮ አሸባሪው ሸኔን በመፋለም ረገድ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ጅምር ተጨባጭ ውጤት መታየቱንም ወጣት አክሊሉ ጠቅሷል።

ሊጉ ይህን ውጤት አጠናክረው በማስቀጠል አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት በማስፈን ልማትና ዕድገትን ለማፋጠን የድርሻቸውን ለመወጣት በየደረጃው ካሉት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አብራርቷል።

ቀደም ብለው የተካሄዱት የውይይት መድረኮች  በወጣቶች ተሳትፎ የተገኙ ጅምር ለውጦችን ለማስቀጠል የሚያስችል አቅም መፈጠሩም ተወስቷል።

የተገኙ ውጤቶችና ግብዓቶችን ገምግመው ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ይህ የምክክር  መድረክ መዘጋጀቱን ወጣት አክሊሉ መግለጹን ሪፖርተራችን ከአዳማ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም