ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡ በአዲሱ ዓመትም እንዲጠናከር የሚደግፉ መሆናቸውን በጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጸ

ጋምቤላ ጳጉሜ 3/2010 በሀገር ደረጃ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፉ መሆናቸውን በጋምቤላ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ። ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወጣት ኡሞድ ኦቻላ ለኢዜአ እንዳለው ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ በነበረው ያለመረጋጋት የዘመን መለወጫ በዓልን ያሳለፈው በስጋት ነበር። በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው ሀገራዊ ለውጥ በዓሉን በአዲስ ተስፋ ለማሳለፍ ተዘጋጅቷል፡፡ የአካባቢያውን ሰላም  በመጠበቅ በሀገር ደረጃ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻውን እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በነበረው የፀጥታ ችግር በዓሉን ደስተኛ ሳይሆን እንዳላሳለፈ ያስታወሰው ደግሞ ወጣት ከኔሳ ደሬሳ ነው። ዘንድሮ በሀገሪቱ የተረጋጋ ሰለም ተፈጥሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከስደት የተመለሱበትና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተቀላቀሉበት ጊዜ በመሆኑ በዓሉን በደስታና በፍቅር ለማክብር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። አቶ ጌታሁን መኮንን በበኩላቸው መንግስት ለታራሚዎች ባደረገው ይቅርታ ከማረሚያ ቤት መውጣታቸውን ጠቅሰው አዲሱን ዓመት ከቤተሰባቸው ጋር በደስታ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። እንደአስተያየት ሰጪው ገለጻ መንግስት በጀመራቸውን የለውጥ፣ የፍትህና የአንድነት ስራዎችን በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ እንዲቀጠል የድርሻቸውን ለማበርከት ዝግጁ ናቸው። በዓሉን አዲሱን ለውጥ ካመጣው መንግስት ጋር በፍቅርና በደስታ ለማከበር መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ባንቲ ኮማል ናቸው። ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ወንዴ ቦንቻም  አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱንና አብሮነቱን እየገነባ ባለበት ወቅት የሚከበር መሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። በዓሉን በአብሮነትና በመደጋፍ በጋራ ለማክበር እየተዘጋጁ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም