ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ግንባር ቀደም ሚናዋን ለመወጣት ትሰራለች

111

ግንቦት 04/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ግንባር ቀደም ሚናዋን መወጣቷን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ።

አፍሪካ ተኩስ የማይሰማባት አህጉር ለመሆን ግብ ብታስቀምጥም የታሰበው ሳይሳካ የግጭት፣ የሰላምና መረጋጋት እጦት የሚታይባት አህጉር ሆና ቀጥላለች።

የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የመከላከያ፣ የፀጥታና ደህንነት ሚኒስትሮችና ወታደራዊ መኮንኖች በአህጉራዊ የሰላምና ፀጥታ ችግሮች ላይ መፍትሔ ለማምጣት ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሲመክሩ ሰንብተዋል።

ዛሬም የመከላከያ፣ ፀጥታና ደህንነት ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ 14ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

በስብሰባው በአፍሪካ ኢ-ሕገ-መንግሰታዊ የመንግስት ግልበጣ ሙከራዎች፣ ሽብርተኝነት፣ የባህር ላይ ወንበዴዎች መበራከት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ፖለቲካዊ ሁከትና ብጥብጦች አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸው ተነስቷል።

የፀጥታና ደህንነት ችግሮችን ለመፍታትም አህጉራዊ የሆነ በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ የተጠንቀቅ ወታደራዊ ኃይልን ከማቋቋም ጀምሮ ዘላቂ ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ተገልጿል።

በጉባኤው ላይ የታደሙት የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፤ ኢትዮጵያ አህጉራዊ የፀጥታና ደህንነት ልዩ ኮሚቴ ስብሰባውን በማስተናገዷ ደስተኞች ነን ብለዋል።

አፍሪካ ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንድትወጣ የጋራ መፍትሔ ለማምጣት መመካከርና በቀጣይነት አብሮ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ለዚህም የመከላከያ፣ ፀጥታና ደህንነት ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴው ስብሰባ ለአህጉሪቱ ባስፈላጊ ወቅት የተካሄደ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በውስጧ ያሉ የፀጥታና ደህንነት ችግሮችን ለማስወገድ እየሰራች  መሆኗን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ከራሷ አልፋ በሶማሊያ የአልሸባብን አሸባሪዎች በመዋጋት በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ዛሬም ድረስ የሰላም ማስከበር ሚናዋን በብቃት እየተወጣች መሆኗን ጠቅሰዋል።

በሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት የሚከሰቱ ሽብርተኝነትና ጽንፈኝነትን ለማስወገድና ፀጥታና ደህንነት በአህጉሪቱ ለማስፈን በግንባር ቀደምነት ስትሰራ መቆየቷንም አስታውሰዋል።

በቀጣይም በአፍሪካ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ሽብርተኝነት እንዲወገድ ዝግጁ ናት ያሉት ዶክተር አብርሃም ግንባር ቀደም ሚናዋንም አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

በስብሰባው ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላም በትብብር መሥራት የሚያስችል ሰነድ እንዲጸድቅ ኢትዮጵያ አቋሟን አንጸባርቃለችም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም