ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ድጋፍ እንዲያደርግ ኮሚሽኑ ጠየቀ

ግንቦት 4/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቀ።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ጋር ተወያይተዋል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የኮሚሽኑን ዓላማና ምስረታ፣ አወቃቀር፣ የአገራዊ ምክክር አሰራር ሂደት፣ የእስካሁኑ ቅድመ-ዝግጅት ምዕራፍ ክንውኖችና ቀጣይ የዝግጅትና ትግበራ ሂደትን አብራርተዋል።

በሕዝብ ጥቆማ የተመረጡ 11 አባላትን ያቀፈው ኮሚሽኑ በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ከታች ወደ ላይ አካታችና አሳታፊ ውይይት በማድረግ አገራዊ መግባባት እውን እንዲሆን ማስቻል ነው ብለዋል።

የኮሚሽኑ ተልዕኮ ይሰምር ዘንድ ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት፣ የቀደሙ ሁለት ኮሚሽኖችን ሰነድ በግብዓትነት መጠቀምና በብሔራዊ ውይይት ልምድ ካላቸው አገራት ተሞክሮ ይቀስማል ብለዋል።

ሌሎች ኮሚሽነሮችም ስኬታማ፡ አካታችና ውጤታማ አገራዊ ምክክር በማድረግ ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ለማንበር ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ያገኘ፣ የተለመደ ልሂቃን ውይይት ሳይሆን ከታኛው ህብረተሰብ ጀምሮ ሁሉን አሳታፊና ሀሳብ የሚንሸራሸርበት፣ በግልፀኝነትና ተጠያቂነት መርሆች የሚመራ ነው ብለዋል።

አገራዊ ጉዳዮች በሚገባ ውይይት ተደርጎባቸው ብሔራዊ ዕርቅን ዕውን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ዝግጀት ምዕራፍ እየገባ መሆኑን ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክሩ የሚመራው ካለምንም የውጭ ጣልቃገብነትና ጥምዘዛ በኢትዮጵያዊያን እንደሆነና ለዴሞክራሲም ትልቅ አሻራ ጥሎ የሚያልፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የሁሉንም ወገን አካታችነት፣ ገለልተኝነት፣ በፋይናንስና መሰል ጉዳዮች ጥያቄዎችን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

በውይይት መድረኩ ኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ለማድረግ የያዘችው ፕሮጀክት ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም በቅጡ ተረድተናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር የቭጊኒ ተርኪን ከኮሚሽነሮቹ ጋር በመወያየታቸው ደስታቸውን በመግለጽ፣ ኮሚሽኑ ብሔራዊ እርቅን እውን በማድረግና የኢትዮጵያን ሕልውናዋን በማረጋገጥ ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ፤ ለተመድ ጠንካራ አባሉ ለሆነችው ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ይደግፋል ብለዋል።

ከኮሚሽነሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬያማ መሆኑን ገልጸው፤ ከኮሚሽኑ ምስረታ ጀምሮ ተመድ ድጋፍ እንዳደረገ በመጥቀስ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከችግር ለማውጣት የራሱ በጎ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በአገራዊ ምክክር ሰላምና መረጋጋት ከተረጋገጠ ለችግር ተጋላጭ ወገኖች መጠን ስለሚቀንስ ለምክክሩ ስኬታማነት ተመድ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አለፕ፤ ኢትዮጵያና ቱርክ በክፉ ጊዜም የሚተሳሰቡ ወዳጅ አገሮች መሆናቸውን ገልጸው፤ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ቱርክ ድጋፏን እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ምክክር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሯ፤ የኢትዮጵያን መልከ-ብዙ ችግሮች በውይይት ለመፍታት ኮሚሽነሮቹ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተገንዝበናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም