ፋውንዴሽኑ በደብረ ብርሀን ከተማ ለተፈናቀዮችና ለሆስፒታል መቋቋሚያ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ፋውንዴሽኑ በደብረ ብርሀን ከተማ ለተፈናቀዮችና ለሆስፒታል መቋቋሚያ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ
ደብረ ብርሃን፤ ግንቦት 4/2014 (ኢዜአ)፡ የወንድም ካሊድ ግብር ሰናይ ፋውንዴሽን በሸኔ የሽብር ቡድን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖችና ለሆስፒታል ማቋቋሚያ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ።
የወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ካሊድ ናስር በርክክቡ ላይ እንዳሉት ድጋፉ ''ከኢድ እስከ ኢድ ለተቸገሩ ወገኖች'' በሚል በደቡብ ፈረንሳይ ከተማ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር የተደረገ ነው።
በሽብር ቡድኑ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ 1 ሺህ ቤተሰብ አባላት የሩዝ፣ ቴምር፣ የለውዝ ቅቤ፣ የምግብ ዘይት ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች መደረጋቸውን ተናግረዋል ።
ፋውንዴሽኑ በተጨማሪም ለደብረ ብርሃን አጠቃላይ ሆስፒታል የተለያዩ መድሃኒቶችን በድጋፍ ማበርከቱን ጠቁመው ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው አመልክተዋል።
በደቡብ ፈረንሳይ ከተማ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተወካይ አቶ ፋሪስ ዓሊ በበኩላቸው ተፈናቃይ ወገኖች ያለባቸውን ችግር ለማቃለል በትብብር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አሁን የተደረገው ድጋፍ የተፈናቃዮችን ጊዜያዊ ችግር የሚያቃልል መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ዲያስፖራውን በማስተባበር የመደገፍ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ከምስራቅ ወለጋ ዞን የተፈናቀሉት አቶ ሀሰን አደም እንደገለጹት በበጎ አድራጊዎች እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ የእለት ጉርሳቸውን መሸፈን አስችሏዋል።
''ለዘመናት ያፈሩትን ሀብትና አካባቢ ለቆ የሰው እጅ ጠባቂ ከመሆን በላይ የከፋ ጉዳት የለም'' ያሉት አቶ ሀሰን መንግስት አካባቢውን ከፀረ-ሰላም ሃይሎች አጽድቶ ወደ ቀደመ ቀያቸው አንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።