የአፍሪካን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሀገራት የተቀናጀ ተግባር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሀገራት የተቀናጀ ተግባር ያስፈልጋል
አዲስ አበባ ግንቦት 04/2014 (ኢዜአ) የአፍሪካን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሀገራት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት የሰላም፣ የደህንነትና የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ ተናገሩ።
አፍሪካ የተደራጀ ጠንካራ የተጠንቀቅ ኃይል እንዲኖርም ይሰራል ተብሏል።
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የመከላከያ፣ ፀጥታና ደህንነት ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ 14ኛ መደበኛ ስብሰባ የህብረቱ አባል ሀገራት የመከላከያ፣ የፀጥታና ደህንነት ሚኒስትሮችና ወታደራዊ አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአፍሪካ ህብረት የሰላም፣ የደህንነትና የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤ አፍሪካ በሰላም እጦትና እርስ-በርስ ግጭቶች እየተፈተነች ነው ብለዋል።
በተለይም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ የመንግስት ግልበጣ ሙከራዎች፣ ሽብርተኝነት፣ ግጭት ቀስቃሽ ጽንፈኝነቶች እየተበራከቱ የአህጉሪቱ ፈተናዎች ከሆኑ ውለው አድረዋል ነው ያሉት።
ከዚህም ባሻገር ሕገ-ወጥ የሰዎች እና የአደገኛ ዕፅ ዝውውር ሌላኛው ድንበር ዘለል የአህጉሪቱን መከራ ያከበደ ወንጀል መሆኑን ገልጸዋል ኮሚሽነሩ።
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የመከላከያ፣ ፀጥታና ደህንነት ልዩ ኮሚቴ የሚያደርገው ስብሰባ በአህጉሪቱ ያሉ የፀጥታና ደህንነት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አቋም እንደሚይዝ ጠቅሰዋል።
ልዩ ኮሚቴው በኢ-ሕገ-መንግስታዊ የመንግስት ግልበጣ እንቅስቃሴዎች፣ በሽብርተኝነትና ጽንፈኝነት፣ ፖለቲካዊ ሽግግር ወቅት በሚፈጠሩ ግጭቶችና በኅብረተሰብ ጤና ዙሪያ በሚከሰቱ የደህንነት ስጋቶች ላይ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጠይቀዋል።
የሴኔጋል የመከላከያ ሚኒስትርና የስብሰባው ሊቀ-መንበር ሲዲኪ ካባ፤ በአህጉሪቱ ያሉ የፀጥታና ደህንነት ችግሮችን በሰከነና በተቀናጀ መንገድ ማስወገድ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ልዩ ቴክኒካል ኮሚቴው የአፍሪካ 2063 አጀንዳ ስኬታማ የሚያደርግ ምክረ-ሀሳቦችን በማውጣት በአፍሪካ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።
አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤ አፍሪካ ከቅኝ ግዛትና ከአፓርታይድ ዘመን ወዲህም የእጅ-አዙር ቅኝ ግዛት፣ ጥላቻንና ሽብርተኝነትን ለማስወገድ ትግል ላይ ናት።
የአፍሪካ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ዘላቂ ልማትን የማምጣት ርዕይ የሚሳካው ለነገ በማይተው ጠንካራና የተቀናጀ የተግባር እርምጃ ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ሀገራት አህጉራዊ ነጻነትን ለማስከበር፣ ድንበሮቻቸውን ላለማስደፈርና የህዝቦቻቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ በጋራ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።
አፍሪካን ከግጭት አዙሪት በማላቀቅ ወደ አዲስ የሰላምና ደህንነት ምዕራፍ ለማሸጋገርም ጠንካራ ውሳኔ ማሳለፍና ጠንካራ የቅንጅት ሥራ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
የመከላከያ፣ ፀጥታና ደህንነት ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴው የአፍሪካን ተጠንቀቅ ኃይል በጋራ ለመጠቀም አህጉራዊና ቀጣናዊ ትብብርን ማሳደግ፣ ተገማችና ዘላቂ የፋይናንስ ድጋፍ መኖሩን ማረጋገጥ እንዲሁም የሰለጠነና ዘመናዊ ትጥቅ የተሟላለት የአፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል እንዲኖር በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት የሴኔጋል መከላከያ ሚኒስትር ሲዲኪ ካባ።
በዚህም የአህጉሪቱ የተጠንቀቅ ኃይል የፀጥታ ችግር ባለባቸው በየትኛውም አካባቢ በፍጥነት ተሰማርቶ አፋጣኝ ሰላምና ፀጥታን የማስፈን ሥራን እንዲያከናውን ልዩ ክትትል እንደሚያደርግም በመጥቀስ።
የመከላከያ፣ ፀጥታና ደህንነት ልዩ የቴክኒክ ስብስባው ሲጠናቀቅ በአህጉሪቱ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች ዙሪያ ጠንካራ የውሳኔ ሀሳብ እንደሚያወጣ ይጠበቃል።