ቀጥታ፡

ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የሀጅና ዑምራ ጉዞ ዳግም ተጀመረ

ግንቦት 04/2014(ኢዜአ)  በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የሀጅና ዑምራ ጉዞ ዳግም መጀመሩን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር  እንድሪስ፤ የሀጅና ዑምራ ጉዞን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የሀጅና ዑምራ ጉዞ ዳግም መጀመሩን ተናግረዋል።

ለ1443ኛ ጊዜ በሚካሄደው የዘንድሮው የሀጅ ጉዞ ልኡካንን ጨምሮ 19 ሺህ 800 ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ መፈቀዱንም ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የሀጅ ጉዞ ታሪክ በርካታ ሙስሊሞች እንዲጓዙ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በመፍቀዱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዑለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚና የሀጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ጄይላን ገለታ፤ ተጓዦች ከሀጅ በኋላ ወደ ዑምራ መሄድ እንዲችሉ ከሳዑዲ ሀጅና ዑምራ ሚኒስቴር ጋር ሥምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚና የሀጅና ዑምራ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ሼህ አህመድ የሱፍ ሊበን በበኩላቸው፤ ለሀጅና ኡምራ ጉዞ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ለበርካታ ዓመታት የነበረውን የጉዞ እንግልት በማስቀረት ከአዲስ አበባ ወደ መዲና ቀጥታ በረራ የሚደረግ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

ለሀጅና ዑምራ የሚጓዙ ሁጃጆች ፓስፖርት፣ የኮሮና ክትባት ማስረጃና ለጉዞ በባንክ በኩል ገንዘብ ያስገቡበትን ሰነድ ማሟላት አለባቸው ብለዋል።

የክፍያው መጠንም ለአንድ ሰው 183 ሺህ 500 ብር መሆኑን ጠቁመው፤ ከዛሬ ጀምሮ ጠቅላይ ምክር ቤቱ በመረጣቸው ባንኮች የተጠቀሰውን ገንዘብ ማስገባት ይችላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ዘምዘም እና ሂጅራ ባንኮች ክፍያ የሚፈጽሙባቸው አማራጮች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በሀጅና ዑምራ ጉዞ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ በጉዞው አይካተቱም ሲሉም ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ውጭ በሀጅ ጉዞ ላይ የተፈቀደለት የጉዞ ወኪል የሌለ በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ በሌሎች እንዳይታለል ሲሉም አሳስበዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም