ቀጥታ፡

ወጣቱ ጉልበትና ዕውቀቱን ሀገርን በሚያሻግሩ ተግባራት ላይ ሊያውል ይገባል- አቶ ፀጋዬ ማሞ

ሚዛን፣ ግንቦት 04/2014 (ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ ጉልበትና ዕውቀቱን ሀገርን በሚያሻግሩ የልማትና ሰላም ግንባታ ተግባራት ላይ ሊያውል እንደሚገባ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞ አስታወቁ።

በቤንች   ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ መፍጠርን ያለመ የወጣቶች የውይይት መድረክ ተጀምሯል ።

አቶ ፀጋዬ በወቅቱ እንዳሉት ሀገሪቱ ከገባችበት የተለያዩ ችግሮች እንድትወጣ የሁሉም ዜጎች አንድነትና መተባበር ወሳኝ በመሆኑ ከምን ግዜውም በላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ ያለውን ዕምቅ እውቀትና ጉልበት በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ ሀገርን ሊያሻግሩ በሚችሉ የሰላምና የልማት ተግባራት ላይ በማዋል ችግሮችን የመፍታት ሀላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል ።

ሀገረ መንግስት ግንባታ የሁሉም ዜጎች ተሳትፎ የሚፈልግ መሆኑን ያነሱት አቶ ጸጋዬ በመተባበር እንጅ በመበጣጠስ የሚገኝ ስኬት እንደሌለ አስገንዝበዋል።

በተለይም ወጣቱ ትውልድ በስሜታዊነት ከመመራት በመራቅ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ነገን አሻግሮ በመመለከት በሰከነ መንገድ ሊጓዝ  እንደሚገባ መክረዋል።

"ኢትዮጵያ በርካታ ተስፋዎች ያሉባት ሀገር ናት" ያሉት አቶ ጸጋዬ "ጸጋዎቿን አውጥተን በመጠቀም የተሻለ ነገን ለማየት ፊታችንን ልማት ላይ ልናደርግ ይገባል" ብለዋል።

"ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ሊረጋገጥ የሚችለው በጠንካራ የልማት እንቅስቃሴ በመሆኑ ያለንን ሀብት በአግባቡ ተጠቅመን ከሰራን ከመልማት የሚያግደን ነገር የለም" ብለዋል።

"በሁሉም መስክ የሚታዩ የልማት ጅምሮችን በጠንካራ የስራ ባህል መምራት የምንችል ከሆነ የኢትዮጵያ ብልጽግና ቅርብ ነው" ስሉ አቶ ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው ምግብን በጓሮዎቻችን የማምረት ስራ ውጤታማ እየሆነ መሆኑን መምጣቱን  ጠቅሰው ጅምሩን አጠናክሮ በመቀጠል ሀገራዊ የኑሮ ውድነትን ማሸነፍ እንደሚገባ አነመልክተዋል።

የዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ጉዳይ ከምንም በላይ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ጠቁመው ሁሉም ሰው ፅንፈኞችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት ሀገርን መታደግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ኃላፊነት የማይሰማቸው የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም አፍራሽ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦችን በመመከት ሀገራዊ ሰላምን ማረጋገጥ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ወጣቱ ትውልድ የማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ መረጃ ሰለባ ከመሆን ራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው የውይይት መድረክ ላይ ከ300 በላይ የከተማዋ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም