በጂንካና አካባቢው አጋጥሞ በነበረው የፀጥታ ችግር የተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጂንካና አካባቢው አጋጥሞ በነበረው የፀጥታ ችግር የተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ ነው
ጂንካ፤ ግንቦት 4/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካና አካባቢው አጋጥሞ በነበረው የፀጥታ ችግር የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ የመልሶ ማቋቋም ግብረ ኃይል አስታወቀ ።
በዞኑ አስቸኳይ ምላሽ መስጠትና መልሶ የማቋቋም ግብረ-ኃይል ተፈናቃዮችን በአጭር ጊዜ መልሶ ለማቋቋም እየተካሄዱ ያሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ ምናሴ ዘውዴ በሰጡት መግለጫ በጂንካና አካባቢው ከሚያዚያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የአደረጃጀት ጥያቄን ምክንያት ማድረግ ፀረ-ሰላም ቡድኖች በፈጠሩት ሁከት የፀጥታ ችግር አጋጥሞ እንደነበር ገልጸዋል።።
የአካባቢውን ሕዝብ የማይወክሉ ጥቂት ፀረ-ሰላም ቡድኖች በፈጠሩት ሁከት ጂንካ ከተማን ጨምሮ በጋዘር፣ ሜፀር፣ ቶልታ እና በርካታ ከተሞች የፀጥታ ችግሮች ተፈጥረዋል።
በፀረ-ሰላም ቡድኖቹ በደረሰው ጉዳት ከ1 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎች የተፈናቀሉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በጂንካ፣ ቶልታና ሜፀር ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ወገኖችን ከጊዜያዊ ሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር ክረምት ሳይገባ በአፋጣኝ ወደ ቀድሞው ኑሯቸው ለመመለስ ዞኑ የተለያዩ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ እየሰራ ነው ብለዋል።
የመልሶ ማቋቋም ስራውን ለማጠናቀቅ 72 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ አመልክተው፤ በገንዘብና ዓይነት ሀብት የማሰባሰብ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል
በዞኑ የሚገኙ አመራሮች ከወር ደመወዛቸው 50 በመቶ እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች ደግሞ 30 በመቶ ለተጎጂዎች ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ከገንዘብ ማሰባሰቡ ጎን ለጎን በዞኑ የሚገኙ ወረዳዎች ለቤት ግንባታ የሚሆኑ ግብዓቶች እንዲያቀርቡ ከመግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ማሰባሰቡን ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በደጋማ አካባቢዎች የሚገኙ በባካ ዳውላ አሪ፣ ደቡብ አሪ፣ ዎባ አሪ እና ሰሜን አሪ ወረዳዎች ሕዝቦች ለመኖሪያ ቤት መስሪያ የሚሆን እንጨት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ ማሌ፣ በናፀማይ፣ ሐመር፣ ዳሰነች፣ ኛንጋቶም እና ሳላማጎ ወረዳዎች ደግሞ ለመኖሪያ ቤት ግንባታው የአሸዋና ድንጋይ ግብዓት እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ መንግሥት ደግሞ የቤት ክዳን ቆርቆሮና የሚስማር ግብዓቶችን ድጋፍ እንደሚደረግ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።
የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ ከግንቦት 3 ቀን 2014 ጀምሮ በቶልታ ከተማ መጀመሩን አቶ ምናሴ ገልጸው፤ ለግንባታው የሚውሉ ግብዓቶች ከየወረዳዎች ወደ ስፍራው እየተጓጓዙ ናቸው ብለዋል።