የኢትዮጵያን ታሪክ ለመካድና እውነታውን ለማዛባት የሚጥሩ አካላት ዓላማቸው በሕዝብ ዘንድ ግጭትና አለመተማመን ለመፍጠር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ታሪክ ለመካድና እውነታውን ለማዛባት የሚጥሩ አካላት ዓላማቸው በሕዝብ ዘንድ ግጭትና አለመተማመን ለመፍጠር ነው
ግንቦት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያን ታሪክ ለመካድና እውነታውን ለማዛባት የሚጥሩ አካላት ሁሉ ዓላማቸው በሕዝብ ዘንድ ግጭትና አለመተማመን ለመፍጠር በማሰብ መሆኑን የባህልና ታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ኃይሌ ሙሉቀን ተናገሩ።
በምድር ላይ የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረባት፤ባለ ብዙ ታሪክና ቋንቋ፤ የሁሉ መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ እንደ ውቅያኖስ ጥልቅ የሆኑ በርካታ ባህላዊና ታሪካዊ መገለጫዎች አሏት።
የራስ-ዳሽን ከፍታና የዳሉል ዝቅታ በውብ መልክዓምድር አጅቧት፤ በራሷ ቀን እየቆጠረች፤ በራሷ ፊደላት እየጻፈች እና በአድዋ ድል የጥቁሮችን ታሪክ እየዘከረች ኢትዮጵያ ዘመናትን ተሻግራለች።
ኢትዮጵያ የባለ ብዙ ታሪኮች ጅረት መሆኗ እየታወቀ አሁን አሁን ታሪኳን ለፖለቲካና ለግል ፍላጎታቸው መጠቀሚያነት የሚክዱና የሚያዘበራርቁ አንዳንድ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች እየተስተዋሉ መሆኑን የባህልና ታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ኃይሌ ሙሉቀን ይናገራሉ።
ዶክተር ኃይሌ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ በተለይም አንዳንድ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ያልነበረ ታሪክ ለመፍጠር፤የነበረውን ደግሞ በክህደት ለማጠቃለል ሲጥሩ ይስተዋላል።
ይሁን እንጂ በአገር ላይ ክህደት መፈጸም በየትኛውም መልኩ ከተጠያቂነትና ከታሪክ ተወቃሽነት የማያስቀር መሆኑን ያስረዳሉ።
በመሆኑም ከራሳችን አልፎ ዓለም የሚያውቀውንና የሚያደንቀውን የኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ይዘቱንና እውነቱን እንደጠበቀ ማስቀጠል የጋራ ኃላፊነታችን መሆን አለበት ብለዋል።
"የአድዋ ታሪክ የእኛ ብቻ ነው፤ የኢትዮጵያ የ3 ሺህ ዓመት ታሪክ የእኛ ብቻ ነው" በሚል የአገርን ታሪክ ለመጠቅለል የሚጥሩ አንዳንድ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ለመነጠል ሲል ታሪክ እያሳሳተና ያልነበረውን እየፈጠረ ሕዝብ ማደናገሩን ቀጥሎበታል ብለዋል።
የአሸባሪው ቡድን ዓላማ በሕዝቦች ዘንድ ቁርሾ በመፍጠር ግጭት እንዲባባስና አገር በመከፋፈል የፖለቲካ ስልጣን ጠቅልሎ ለመያዝ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን ታሪክ አዛብቶ የማቅረብ ዝንባሌ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መምጣቱን የጠቆሙት ዶክተር ኃይሌ ባልተገባ መልኩ የተፈጸሙ ታሪኮችንም ቢሆን ለአሁኑ ትውልድ መማሪያ ማድረግ እንጂ ያለፈን ታሪክ የግጭት ምክንያት ማድረግ አይገባም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ እሴት ያለውና በጋራ ታሪክ ሰርቶ አገር ያቆየ በመሆኑ ለመከፋፈልና ለመነጣጠል የሚደረጉ ጥረቶችን ሊታገል ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የማይደበዝዝና የማይነጥፍ የታሪክ አሻራ ለማስቀጠል፣ እሴትና ባህሉን ለማስጠበቅ በጋራ መቆም አለብን ሲሉ መክረዋል።
የአገርን ታሪክ የሚሸረሽሩና ለማዛባት የሚጥሩ አካላትን ደግሞ መንግሥት በዝምታ ሊያልፋቸው አይገባም ብለዋል ዶክተር ኃይሌ።