ቀጥታ፡

አዲስ ዓመት አምናና ዘንድሮ በነዋሪዎች እይታ

አዲስ አበባ  ጳጉሜ 2/2010 በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት የሰዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ ተዛዋውሮ የመኖርና በአንድነት የመኖር ህልውና ሲፈታተን ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደሥልጣን ከመጡ በኋላ ግን የታየው አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት ተስፋ እንዳጫረባቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። ባለፈው ዓመት በዓልን በተረጋጋ ሁኔታ ማክበር ይቅርና ለህይወታችንም "እየሰጋን ነበር ይላሉ" የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች። በአገሪቷ ሠላምን ለማምጣት በተሰራው ሥራም ዘርፈ ብዙ ውጤቶች እየተገኙ መሆናቸው እንዳስደሰታቸውም አውስተዋል። "አሁን ያገኘነው ሠላም ከበፊቱ ጋር የሚነጻጸር አይደለም፤ አሁን በዓሉንም ያለሥጋት ለማክበር ተስፋን ሰንቀናል" ሲሉም ተደምጠዋል። አቶ ተክሉ ተፈራ እንዳሉት  አምና መሽቶ እስከሚነጋ ድረስ ሀሳብ ነበር ዘንድሮ ግን በጥሩ ሁኔታ ስላለን እግዚአብሄርን እናመሰግነዋለን  ፤ይሄን ያበበውን አበባ  ፍሬ አፍርቶ ጥሩ ሆኖ ለማየት ያብቃን ብለዋል፡፡ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ማሞ በበኩላቸው ''አምና ካቻምና ባጣም ስጋት ነበር፤  ወንድሞቻችን በየአካባቢው በየክፍለ አገሩ ወጥተው እስከሚገቡ በጣም እንሰጋለን፤ አሁን ትልቁ ነገር የምንመኘው ለመንግሥታችን እድሜና ጤና እንዲሰጥልን አገሩ ሠላም እንዲሆንልን በየክልሉ ሁሉ ሠላም እንዲሆን እንፈልጋለን።” አዲሱን ዓመት አቅም በሚፈቅድ መጠን ከአከባቢው ነዋሪ ጋር በመረዳዳትና በአንድነት ለማክበር ዝግጁ መሆናቸውንም አስተያየት ሰጪዎቹ ለኢዜአ ገልጸዋል። ወይዘሮ ጥሩወርቅ አክለውም በሃዘንም ሆነ በደስታ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተረዳድተው እንደሚያሳልፉ ገልፀው ወላጅ አልባ የሆኑ ህጻናትን  እንዳቅማቸው በመደገፍ አዲሱን አመት እንደሚያሳልፉ ገልፀዋል፡፡ ወጣት መላኩ ክብረት በበኩሉ  “በልማቱም ፣በመደመሩም በሁሉም ነገር አብረን እጅ ለእጅ ተያይዘን አገራችንን ሠላሟን፣ ጸጥታዋን በማረጋገጥ በኩል አዲሱን ዓመት እንቀበላለን ብዬ ተስፋ  አደርጋለሁ። “ብሏል                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም