ቀጥታ፡

አውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ ዘርፍ ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር ያጠናክራል

ግንቦት 03 /2014(ኢዜአ) የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ ዘርፍ ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰራ በኢትዮጵያ የኅብረቱ ተወካይ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ገለጹ።

አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የአውሮፓ ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በርካታ ተግባራት እያከናወነ ነው።

በተለይም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ እያበረከተች ያለውን ግንኙነት ተከትሎ ኅብረቱ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   

ይህንንም ተከትሎ አውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ሥምምነት እ.አ.አ በ2016 መፈረሙንና ሥምምነቱንም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና የወቅቱ የአውሮፖ ኅብረት ፕሬዝዳንት ጄን ክላዱ ጁንኬ ናቸው በቤልጀም ብራስለስ የተፈራረሙት።

ሥምምነቱም የጋራ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን በጋራ እልባት ለመስጠትና የሁለትዮሽ ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑን በማብራራት ኅብረቱ ይህንንም ስትራቴጂካዊ ሥምምነት በዓለም ላይ ከጥቂት አገራት ጋር ብቻ እንዳለው ጠቁመው ኢትዮጵያም ከእነዚም አገራት መካከል አንዷ መሆኑን ነው ያስረዱት።  

ይህም ኅብረቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በመላው አፍሪካ በፖለቲካው መስክ እያደረገች ያለውን  አስተዋጽዖ ከግምት ያስገባ ትልቅ ውሳኔ መሆኑን ጠቁመዋል።   

ኢትዮጵያ በቀጠናው ለበርካታ ዓመታት በመንግሥታቱ ደርጅትና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በተሰማሩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላትና ኅብረቱም ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን በፖለቲካው መስክ ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።  

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ኅብረቱ ጣልቃ እንደማይገባ የገለጹት አምባሳደሩ ኅብረቱ የመንግሥታቱ ድርጅትና ዓለም አቀፍ መርሆዎችን እሴቶች ያከብራል ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረትና የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ባካሄዱት ዓመታዊ የፖለቲካ ውይይት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከሥምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም