በጂንካና አካባቢው አጋጥሞ በነበረው የሰላም ችግር እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ 824 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጂንካና አካባቢው አጋጥሞ በነበረው የሰላም ችግር እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ 824 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
ጂንካ፤ግንቦት 3/2014 (ኢዜአ)በጂንካና አካባቢዋ አጋጥሞ በነበረው የሰላም ችግር እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ 824 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ አስታወቀ።
የደቡብ ኦሞ ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ለማ ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ኃላፊው በሰጡት መግለጫ ባለፈው ወር በጂንካና አካባቢው የአደረጃጀት ጥያቄን ሰበብ በማድረግ በጥቂት ፀረ-ሰላም ቡድኖች በፈጠሩት ሁከት የሰላም ችግር አጋጥሟል።
የአካባቢውን ማህበረስብም የማይወክሉ እነዚህ ፀረ-ሰላም ቡድኖች በፈጠሩት ሁከት 147 ያህል መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች ወድመዋል ብለዋል።
ኃላፊው በመግለጫቸው በዚህም ሳቢያ ከ1 ሺህ 500 በላይ የጂንካ፣ የጋዘር፣ የሜፀር፣ የቶልታና የበርካ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ተጎጂዎች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ አስቸኳይ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
በወቅቱ የተከሰተውን ሁከት ሰላም አስከባሪዎች በጋራ ባቋቋሙት ግብረ ኃይል ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እንደተቻለ አስታውቀዋል።
የክልሉ የወንጀል መርማሪ ቡድን ከዞኑ የምርመራ ቡድን ጋር በመቀናጀት በወንጀል ድርጊቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 824 ግለሰቦችም በህግ ጥላ ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የአካባቢዎቹ ሰላም እየተመለሰ በመሆኑ የዕለት ተዕለት ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን የብዝሃ-ባህሎች መገኛና ትንሿ ኢትዮጵያና በሰላም ተምሳሌትት የሚትታወቅ መሆኗን ኃላፊው ገልጸዋል።
ይህን በጎ ገፅታዋን መልሶ የመገንባትና ወደ ሰላም ተምሳሌትነቷ የመመለስ ስራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ከሚገኙ የኃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከጎሳ መሪዎች የተወጣጡ የዕርቀ ሰላም ኮሚቴዎች ችግሩን ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን አቶ መላኩ አስታውቀዋል።