ቀጥታ፡

ሰላምን በማስፈንና ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ለመጭው ትውልድ የበለፀገች ኢትዮጵያን እናስረክባለን - አቶ ደመቀ መኮንን

ባህር ዳር ግንቦት 03/2014 (ኢዜአ) "ሰላምን በማስፈንና ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት ለመጭው ትውልድ የታፈረችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ታሪካዊ ሃላፊነታችን የምንወጣበት ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

ʺበሕግ ማስከበርና በሕልውና ዘመቻው የተከፈለ መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በዘመቻው የላቀ ሚና ላበረከቱ የፀጥታ አባላት እውቅናና የማዕረግ እድገት በባህር ዳር  ትላንት አመሻሹ ላይ ተሰጥቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ  በፕሮግራሙ ላይ እንዳሉት "ከሃዲው ቡድን ጠላቶቻችን በሚሰጠው ተልዕኮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያደረገው ሙከራ ከሽፏል።"

አሸባሪው ህውሃት የፈጸመው ወረራ ምንም በማያውቁ ንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ፣ የሃብት ዘረፋና ውድመት ሊረሳ  የማይችል ግፍና በደል መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ሰላምና ፀጥታን በማስጠበቅ የህዝባችን ደህንነት በማስከበር የልማት ስራዎችን በአግባቡ በመከወን ጠንካራ ኢኮኖሚ የምንገነባበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ሰላም በማስፈንና ኢኮኖሚን በማሳደግ ለመጭው ትውልድ የታፈረች፣ የተከበረችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ህዝብ በጋራ ሊረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

በክህደት የተፈጸመብንን ወረራ ለመመከትና በድል ለመወጣት መላ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ባንድነት በመንቀሳቀስ አሸባሪው ህወሃትን ድባቅ መትቶ ወደ መጣበት መመለስ መቻሉን አስታውሰዋል።

"በሃይማኖት፣ በብሄርና አካባቢን መሰረት ያደረጉ መቃቃሮችንን ለመፍጠር የሚደረጉ ቅስቀሳዎችና ትንኮሳዎችን ለደቂቃም ቢሆን ባለመዘናጋት በአብሮነት ክንዳችን መመከት ያስፈልጋል"ብለዋል።

"አሁን ላይ ወደ ብልጽግና ጉዞ ለመሻገር እየተደረገ ያለውን ጠንካራ ስራ ለማደናቀፍ ጠላቶች የሞት ሽረት ትግል ላይ ናቸው" ሲሉ ጠቁመዋል።

ወራሪው ሃይል ካለፈው ጥፋቱ ባለመማር ለዳግም ወረራ እያደረገ ያለውን ዝግጅት የትግራይ ህዝብና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያስቆሙት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ይህ ካልሆነ ግን ቡድኑ ለሚፈጽመው ትንኮሳና ለዳግም ወረራ እንቅስቃሴው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በመሰለፍ የማያዳግም እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ሁሉም አካል ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ በበኩላቸው ወራሪው ቡድን የአማራ ክልልን ዳግም ለመውረር ጦርነት እየጎሰመ በመሆኑ የማያዳግም ቅጣት ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በሚሰጠው የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራም ጀግኖችንና የጀግና ቤተሰቦችን በመሸለም ሁሉንም የፀጥታ ሃይልና ደጀን የሆነውን ህዝብ ለቀጣይ ግዳጅ ዝግጁ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

እውቅናና ሽልማቱ በህግ ማስከበርና በህልውና ዘመቻው የላቀ ግዳጅ ለፈጸሙ የፀጥታ ሃይሎችን ለማበረታት ያለመ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ናቸው።

በዚህም በአመራር ሰጭነት፣ በተዋጊነት፣ በሎጅስቲክ አቅርቦትና ሌሎች ጦርነቱን በሚደግፉ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ የፀጥታ አካላትን ለማበረታት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ መድረክ እውቅናና ምስጋና የሚሰጣቸው አካላት ብቻ ናቸው ጀግኖቻችን ማለት እንዳልሆነ መላ ህዝባችን ሊገነዘብ ይገባል ያሉት አቶ ደሳለኝ በቀጣይ እስከ ታች  ባለው አደረጃጀት የሚቀጥል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ትናንት ምሽት ለጠላት እጅ ያልሰጡ ቀበሌዎች፣ የልዩ ሃይልና የመደበኛ ፖሊስ እንዲሁም የማረሚያ ቤቶች፣ ጀብዱ የፈጸሙ ብርጌዶችና ሻለቆች የማዕረግ እድገትና የአይነት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በዛሬው እለትም ፕሮግራሙ የተለያዩ ክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የእውቅና ስነ ስርዓቱ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም