ቀጥታ፡

በሻሸመኔ ከተማ እና አከባቢዋ በሁለት ዙር የሚሰጥ የኮሌራ መከላከያ ክትባት ተጀመረ

ግንቦት 3/2014 /ኢዜአ/ በሻሸመኔ ከተማ እና አከባቢዋ በሁለት ዙር ለሚሰጠው የኮሌራ መከላከያ ክትባት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ።

ክትባቱ በመጀመሪያ ዙር ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን፤ በሁለተኛ ዙርም ደግሞ ከግንቦት 19 እስከ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥም ተገልጿል።

ክትባቱን የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት እና ሌሎች አካላት በጋራ የሚሰጡ መሆኑ ተገልጿል።

የሻሸመኔ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ መሃመድ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በከተማዋ እና አከባቢው የሚሰጠው ክትባት ከ100 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ተደራሽ የሚሆን ነው ብለዋል።

ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን የሚያገኙ መሆኑን ጠቅሰው አንድ ሰው በሁለት ዙር ይህን ክትባት የሚያገኝ መሆኑም ተነግሯል።

የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ ወሾ ከድር በበኩላቸው የህዝብ ልማት የሚረጋገጠው የህዝቦች ጤና ሲጠበቅ መሆኑን ተናግርዋል።

አስተዳደሩም የህብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ እና ለህብረተሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንዳሉትም፤ ኮሌራ ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ኢንስቲትዩታቸውም የኮሌራ በሽታን በ2030 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ለማጥፋት እየሰራ መሆኑ የተናገሩት ዳይሬክተሩ በዛሬው ዕለት የተጀመረው ክትባትም የዚህ አካል ነው ብለዋል።

በሁለት ዙር በሚሰጠው የክትባት መርሃ ግብርም በሻሸመኔ ከተማ እና ሻሸመኔ ወረዳ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ክትባቱን የሚያገኙ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ የግልና የአከባቢውን ንጽህና በመጠበቅ ይህን በሽታ መከላከል እንደሚገባም ተገልጿል።

አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ክትባት እና መድሃኒቶችን በአገር ውስጥ ለማበልፀግ የተቋቋመ ተቋም ነው።

በሻሸመኔ ከተማ በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ሌሎች እንግዶች እና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም