ሶስት የመንግስት ተቋማት የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ሶስት የመንግስት ተቋማት የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በጋራ ለመስራት ተስማሙ
ግንቦት 3 /2014(ኢዜአ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴርና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለግንባታ ስራ ከሚውሉ ግብዓቶች መካከል እስከ 65 በመቶ የሚሆነውን ኢትዮጵያ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት የምታስገባ ሲሆን ከውጭ የሚገባው የግንባታ ግብአት ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጭ እየዳረገና ለግንባታ መጓተትም ምክንያት መሆኑ ይነገራል።
የኮንስትራክሽን ዘርፉ ቢያድግም ከውጭ የሚገቡ የግንባታ እቃዎች ዋጋ መናር ፈተና እየሆነ በመምጣቱ የመፍትሄ አማራጮችን መከተል ተገቢ መሆኑ ይታመናል።
ለዚህም ሲባል የከተማና መሠረተልማት ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር እና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የከተማና መሰረተልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፣ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ለሊሴ ነሜ ተፈራርመዋል።
በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የግንባታ ዘርፍ ከውጭ የሚገቡ የግንባታ እቃዎችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካትና የውጭ ምንዛሬ ወጪ በመቀነስ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ እድገት የስምምነቱ ጠቀሜታ የላቀ ነው ተብሏል።
ከውጭ የሚገቡትን በሀገር ውስጥ ማምረት እንዲቻል የግብዓት ማዕድናቱ በበቂ መጠን መኖሩን ማረጋገጥና የግንባታ ፕሮጀክቶች ግብዓቶችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመፍጠርም በጋራ ይሰራሉ።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት ፤ የግንባታ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም የተለያዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች ዘርፍ ለሀገሪቱ ማበርከት ያለበት ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ላይ ጫና ፈጥሯል።
ለግንባታ ከሚውሉ ግብዓቶች እስከ 65 በመቶው ከውጭ የሚገባ በመሆኑ የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ታክሎበት ችግር እየገጠመው ይገኛል ሲሉ ገልጸው በዘርፉ ላይ የተደቀነውን ጫና እና ችግሩን ለማቃለል የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም የከተማና መሠረተልማት ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር እና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ለሊሴ ነሜ፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ እንዲያመርቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተቋማቱ የጋራ ስምምነት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የማዕድን አምራቾች ለግንባታ ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን እንዲያመርቱ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲሚንቶ፣ ሴራሚክ፣ ግራናይት፣ ብርጭቆና ሌሎችም ምርቶች በሀገር ውስጥ በብዛት ለማምረት ያለንን የማዕድን አቅም በማጥናት ወደ ተግባር ለመግባት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የተቋማቱን ስምምነት ገቢራዊነት የሚከተታተል የጋራ ግብrኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ የሚገባ መሆኑም ታውቋል።