ቀጥታ፡

የተጀመረው ለውጥ እንዲሳካ ህዝቡ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2010 በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ እንዲሳካ ህዝቡ ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባሰባሰበው ግብረ መልስ አመለከተ። አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣበት ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፍቅር፣ የመደመር፣ የመቻቻልና የይቅርታ ጥሪን በማብሰር በአገር ውስጥና በውጭ ላሉ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ የለውጥ እንቅስቃሴዎች መምጣታቸውን አመልክቷል። መጪው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መላው ህዝብ በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል በአዲስ መንፈስ ለአገር ግንባታ፣ ለዘላቂ ሰላምና ዋስትና ላለው ዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር ድርሻውን መወጣት እንዳለበት ግብረ መልሱ ጠቁሟል። “በፍቅር ተደምረን በይቅርታ እንሻገር” የሚለውን የአዲሱን 2011 ዓመት መሪ ሀሳብ በተግባር ለመተርጎም ህዝቡ ያለውን ተነሳሽነት ለመፈተሽ ጽህፈት ቤቱ ግብረ መልስ ማካሄዱን ገልጿል። የግብረ መልስ ጥንቅሩ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሶማሌ ክልል በስተቀር ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ ሰባቱ ክልሎች የተሳተፉ ሲሆን በመረጃ አሰባሰብ ሂደቱም 916 አስተያየት ሰጪዎች መሳተፋቸውን አስታውቋል። አስተያየት ሰጪዎቹ “ባለን ሙያ ህዝብ ለማገልገልና ለውጡን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመደገፍ ዝግጁ ነን”፣ “የለውጡ እንቅፋት የሆኑትን በአስተሳሰብና በተግባር መታገል ይጠበቅብናል”፣ “አዲሱን ዓመት በቀልን ትተን እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ልማት መግባት”፣ “ለለዉጥ እንቅስቃሴ የሚጠቅሙ አዳዲስ ሀሳቦችን ማቅረብ” እና  “የመጣውን ለውጥ እንዳይቀለበስ የለውጡን መልዕክት ማስተጋባት ይጠበቅብናል” የሚሉ ምላሽ አስጥተዋል። እንዲሁም “የተጀመረውን ለውጥ ለማጠናከር በኔትወርክና ያለብቃት የሚመደቡ አመራሮችን በመማስወገድ በልምድና በብቃት ላይ የተመሠረተ የአመራር ስምሪትና ሹመት መስጠት”፣ “ህገ-ወጥነት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ አጠናቅሮ ማስቀጠል”፣ “የዜጎች ነፃ አስተሳሰብን ማጎልበት የሚሉት የተሰጡ ምላሾች ናቸው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ተጨባጭ መረጃ ማቅረብ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር”፣ “መቻቻል፣ መደማመጥ፣ መከባበርና ኀብረተሰቡ ሞጋች ሆኖ ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታ መፍጠር”፣ “የህግ በላይነትን ማክበርና ሰላም ማስፈን፣ የመንግስት ሀብት በመዝረፍ ላይ ያሉትን መያዝ” የሚሉትም እንዲሁ፡፡ በተጨማሪም “በየደረጃው ያሉ አመራሮች የህዝብ አገልጋዮች እንጂ ስልጣናቸውን ተጠቅመው እንዳይበድሉ ክትትል ማድረግ”፣ “ህዝብን በቅንነት፣ በታማኝነትና በእዉቀት መምራት ያልቻሉ አመራሮች ሙሉ በሙሉ መነሳት አለባቸዉ”፣ “የህዝብ ይሁንታን ማግኘት የሚችሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲጠናከሩና የፖለቲካ ምህዳሩ ማስፋት” እንዲሁም “የህዝብን ሀብት የመዘበሩ፣ የሰውን ህይወት ያጠፉ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ውለው በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ” በአዲሱ ዓመት ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንደሆነም በግብረ መልሱ ተጠቅሷል። እንዲሁም “የህግ የበላይነት እንዲከበር ማድረግ”፣ “ስራ-አጥ ወጣቱንና ድሃ የኀብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ ስራ መስራት”፣ “ዘረኝነትና ብሔር ተኮር ጥቃት ማስወገድ”፣ “ህገ-ወጥ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝውውር የሚያካሄዱ እንዲሁም ለውጡን በሚያደናቅፉ አካላት ላይ አስቀድሞ እርምጃ መውሰድ”፣ “የኑሮ ውድነት እንዲረጋጋ ትኩረት ሰጥቶ መስራት” በአዲሱ ዓመት በትኩረት የሚከናወኑ ተግባራት እንዲሆኑ አስተያየት ገልጸዋል፡፡ “ሙስናንና ብልሹን አሰራር ለማስቀረት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተገቢ ሚና መጫወት” እንዲሁም “የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አዳዲስ ፕሮጀክቶች ለማስጀመር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠርም” ሌሎች የአዲሱ ዓመት የትኩረት አጀንዳዎች እንዲሆኑ በአስተያየት ሰጪዎቹ መጠቀሳቸውን ጽህፈት ቤቱ የላከው መግለጫ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም