የ"ኢንተርፕሪነር" ስልጠና ከስራ ጠባቂነት ይልቅ ስራ ፈጣሪ ለመሆን ያግዘናል- ሰልጣኝ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የ"ኢንተርፕሪነር" ስልጠና ከስራ ጠባቂነት ይልቅ ስራ ፈጣሪ ለመሆን ያግዘናል- ሰልጣኝ ወጣቶች

ሀዋሳ፤ ግንቦት 2/2014 (ኢዜአ) እየተሰጣቸው ያለው የ"ኢንተርፕሪነር" ስልጠና ከስራ ጠባቂነት ይልቅ ስራ ፈጣሪ ለመሆን እንደሚያግዛቸው በሃዋሳ ከተማ ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉ ወጣቶች ተናገሩ፡፡
ዳሽን ባንክ "ዳሽን ከፍታ" የተሰኘ የስራ ፈጠራ ውድድር ለማካሄድ አዳዲስ የንግድ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በንግድ ስራ ፈጠራና አመራር ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
ከሰልጣኞቹ መካከል በሃዋሳ ዪኒቨርሲቲ የኤሌክትሮ መካኒካል ኢንጅነሪንግ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ ቅድስት ተሾመ ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት፤ ወጣቱ ከተመረቀ በኋላ ስራ ማግኘት ችግር እንደሆነ ተናግራለች፡፡
በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚሰጡ የስራ ፈጠራና የስራ ክህሎት ስልጠና ችግሩን ለማቃለል የሚያስችሉ አስተሳሰቦችን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ነው የገለጸችው፡፡
ኢንተርፕሪነር የ(ስራ ፈጣሪነት) ስልጠና መሰጠቱ ወጣቱ ከስራ ጠባቂነት ይልቅ ስራ ፈጣሪ በመሆን ከራሱ አልፎ ለሀገሩ የሚጠቅም ችግር ፈቺ ተግባራት ለመፍጠር የሚረዳ ነው ብላለች።
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከተመረቀ በኋላ ላለፉት አራት ዓመታት የራሱን የንግድ ሃሳብ በማመንጨትና ስራ በመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ገረማቸው ዋጋዬ ነው።
ባንኩ ባዘጋጀው የንግድ ስራ ፈጠራ ውድድር ላይ ለመሰማራት ስልጠናውን እየወሰደ መሆኑን ገልጾ፤ እድሉን ተጠቅሞ ለሃገር የሚጠቅም ስራ ለመስራት መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡
ወጣቱ በትምህርት ያገኘውን እውቀት በተግባር ለማሳየት የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ስራ ላይ መሰማራት እንዳለበት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች ተቀጣሪ ሆነው ከመስራት ይልቅ ስራ ፈጣሪ በመሆን የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ መስራት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብሏል።
በቀጣይም መስራት በሚፈልገው አዲስ የንግድ ስራ ላይ ባንኩም ሆነ የመንግስት አካላት የገንዘብና የተለያዩ ድጋፎች እንዲያደርጉለት ይፈልጋል ወጣት ገረማቸው፡፡
በዳሽን ባንክ የሃዋሳ ቀጠና ስራ አስኪያጅ አቶ ጴጥሮስ ሞገስ፤ መንግስት ስራ አጥነትን ችግር ለማቃለል የሚሰራውን ለመደገፍ አዳዲስ የስራ ፈጣሪዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከፍተኛ ብድር በሚወስዱት ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ተመራቂዎችንና በትንሽ ገንዘብ መደገፍ የሚችሉ የፈጠራ ክፍሎት ያላቸውን ወጣቶችን አሰልጥኖ ወደስራ በማሰማራት ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡
በሀገሪቱ ስድስት ከተሞች አዳዲስ ስራ ፈጣሪዎችን ለማምጣት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ በዳሽን ባንክ የገበያና ልማትና የደንበኞች አገልግሎት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኝ ጌታቸው ናቸው፡፡
"ዳሽን ከፍታ" በተሰኘ የስራ ፈጠራ ውድድር ፕሮግራም ባንኩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የጀመረው ተግባር መንግስትን እየሰራ ያለውን ተግባር ለመደገፍ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ወጣቶች በስራ ፈጠራ ክህሎታቸው ተወዳድረው በማሸነፍ ወደተግባር እንዲገቡ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከየከተሞቹ የተመረጡ የመጨረሻዎቹ ሶስት አሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት እንደሚያገኙ አስታውቀዋል፡፡
ለወጣቶቹ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ለአምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ተግባር ተኮር መረሃ ግብር እንደሚኖርም የኢዜአ ሪፖርተር ከሀዋሳ ዘግባለች፡፡