ገበያውንና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ በአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

358

አሶሳ ፤ ግንቦት 2 / 2014 (ኢዜአ) በፍጆታ ምርቶች ላይ እየጨመረ የመጣውን የገበያ ዋጋና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

የከተማዋ አስተዳደር በበኩሉ ፤ገበያውን ለማረጋጋትና የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የ100 ቀናት እቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን ሲገልጽ፤ ክልሉም ችግሩን ለመፍታት ግብረሃይሎች ተቋቁመው እርምጃ እየተወሰዱ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከአሶሳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኦብሳ ኢዶሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በከተማው  በተለያዩ የፍጆታ ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡

እንዲሁም መንግስት በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ መሆኑን ቢገልጽም ነዳጅ ጨምሯል በማለት የባጃጅ ታክሲዎች ትራንስፖርት ታሪፍ ከአምስት ብር ወደ 20 ብር  ከፍ በማድረጋቸው ለመጠቀም መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከገበያ ዋጋ ጋር ተያይዞ ያስከተለባቸውን የኑሮ ውድነትና ሌሎችንም  ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በቅርቡ  የከተማውን ነዋሪ አወያይቶ የገባውን ቃል ወደ ተግባር  በመቀየር መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

አቶ ናስር መሃመድ በበኩላቸው፤  አሁን ያለው የኑሮ ውድነት እየተባባሰ የሚገኝበት ዋነኛ ምክንያት በአካባቢው የተሟላ ሠላም አለመኖሩ ይመስለኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን አጠናክረን ሠላማችንን መመለስ አለብን፤  ከጎረቤት ሀገራት ተፈናቅለው በሃገራችን ከሚገኙ የውጪ ዜጎች ችግር መማር አለብን ነው ያሉት፡፡

በዚህ ረገድ መንግስት ብዙ ስራ እንደሚጠብቅበት ተናግረዋል።

አሁን ያለው የኑሮ ውድነት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኘው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ሃሊማ ጀሃድ ናቸው።  

ሽንኩርትና ቲማቲምን ጨምሮ በሌሎችም  አትክልቶች  ላይ  የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንደሚታይ ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት በከተማው የሚገኙ ስራአጥ ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ ገበያ ማረጋጋት ስራ ቢያሰማራ ችግሩን ለማቃለል  ያግዛል  ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ ደግሞ ለራሱ ብቻ ከማሰብ እና ወገኑን በአላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ከመጉዳት ሊቆጠብ እንደሚገባ ወይዘሮ ሃሊማ ተናግረዋል፡፡

እየጨመረ የመጣውን የገበያ ዋጋና የኑሮ ውድነትን  ለማረጋጋት መንግስት የገባውን ቃል በመተግበር  የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ነው ነዋሪዎቹ የጠየቁት።

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪ እና ትራንስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ባበክር ሃሚድ በበኩላቸው ፤ መምሪያው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት  የ100 ቀናት እቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በከተማው ህብረተሰቡን በስፋት ቅሬታ የሚያነሳበትን የአንድ ኪሎ ጥሬ ስጋ ዋጋ ተመን 400 ብር እንዲሆን መደረጉን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

አስተዳደሩ በጥናት ላይ ተሞርክዞ ያወጣውን ይህንኑ የዋጋ ተመን የተላለፉና  የኪሎ መጠንን ያጎደሉ አምስት ሉኳንዳ ቤቶች ታሽገው ንግድ ፍቃዳቸው ጭምር እንደተነጠቀ አስታውቀዋል፡፡

ጉዳያቸው በህግ መታየት የጀመረ እንዳለ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ተመርተው በየጊዜው ዋጋቸው እየናረ የሚገኙ ሽንኩርት እና ቲማቲምን ጨምሮ ሌሎች የጓሮ አትክልቶችና   ፍጆታ ምርቶችን ዋጋ ለማረጋጋት በቅርቡ አምራቹን እና የከተማውን ማህበረሰብ በቀጥታ የሚያገናኝ ግብይት ይጀመራል ብለዋል፡፡

የከተማ ታክሲን ከታሪፍ በላይ በማስከፈል በተደጋጋሚ በማስጠንቀቂያ ታልፈው ሊታረሙ ያልቻሉ የባጃጅ ታክሲ አሽከርካሪዎች ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ ከ100 ሺህ ብር በላይ መቀጣታቸውን አብራርተዋል፡፡

ነዋሪው በግቢው የጓሮ አትክልትን ጨምሮ የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ ለሜሳ ዋውያ፤ በክልሉ የዋጋ ንረትን ፣ የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት የሚቆጣጠሩ ሁለት ኮሚቴዎች ተዋቅረው ስራ መጀመራቸውን  ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የወንጀል ምርመራ ቡድን ጨምሮ ከተማ አስተዳደር፣ ፖሊስ፣ ገቢዎች ባለስልጣን እና ሌሎች ችግሩን በመከላከል ቁልፍ ድርሻ ያላቸውን ተቋማት በግብረሃይሎቹ  እንደተካተቱ አስረድተዋል፡፡

ግብረ ሃይሎቹ በተቋቋሙ የመጀመሪያ 10 ቀናት በ420 የንግድ ተቋማት ላይ ጥናት ማድረጋቸውን ሃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ከነዚህም ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ  20 የንግድ ተቋማት ሲታሸጉ ሰባቱ ደግሞ እያዳንዳቸው እስከ 14 ሺህ ብር መቀጮ መክፈላቸውን አቶ ለሜሳ ጠቁመዋል፡፡

የንግድ ተቋማት ላይ ቅጣት የተጣለው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ፣ ያለፈቃድ ሲነግዱና ያለደረሰኝ ግብይት ሲያካሂዱ  በመገኘታቸው እንደሆነ አመላክተዋል፡፡  

ያለዋጋ ዝርዝር ሽያጭ ሲያካሂዱ የነበሩ 350 የንግድ ድርጅቶች ላይ ደግሞ ቁጥጥር በማድረግ የዋጋ ተመን ለሸማቹ ማህበረሰብ በግልጽ ለጥፈው ሽያጭ እንዲያካሂዱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በጸጥታ ችግር ነዳጅ ወደ አካባቢው የሚገባው በጸጥታ አስከባሪዎች ታጅቦ ነው ያሉት አቶ ለሜሳ ፤ይህም የአቅርቦት እና ስርጭት አለመመጣጠን በማስከተል ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡

በከተማው በጥቁር ገበያ የሚሸጠው ቤንዚን እና ናፍጣ ግን ከአጎራባች እና ከአዲስ አበባ በድብቅ የሚገባ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታዩ የሚገኙ ማደያዎች እና ግለሰቦች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

የፋብሪካ ውጤቶችን ዋጋ ጭማሪን ጨምሮ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር  ሚኒስቴር፣ ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች እና ማደያ ባለቤቶች ጋር እየተሠራ መሆኑን ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ሃገራዊ የሆነውን የኑሮ ውድነት ችግር በዘላቂነት ለመከላከል ሸማቹም የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥመው ግዥ ባለመፈጸምና ጥቆማ ከማድረግ ጀምሮ መረጃ በመስጠት ግብረሃይሉን በመደገፍ ለመብቱ መቆም እንዳለበት ሃላፊው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም