የሶማሌ ክልል የሰንደቅ ዓላማውን ምልክት ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
የሶማሌ ክልል የሰንደቅ ዓላማውን ምልክት ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ወሰነ
ጅግጅጋ ጳጉሜ 2/2010 የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ አሁን እያገለገለ ያለውን የክልሉን ሰንደቅ ዓላማ ምልክት ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ወሰነ። ምክር ቤቱ ሰንደቅ ዓላማው ወደ ቀደመው ይዞታው እንዲቀየር የወሰነው አሁን ጥቅም ላይ ያለው ሰንደቅ ዓላማ በቀድሞው ርዕሰ-መስተዳደር ፍላጎት የወጣና ህዝብ ስላልመከረበት እንደሆነም ተመልክቷል። የቀድሞው ሰንደቅ ዓላማም ከነገ ጀምሮ በመንግስት መስሪያ ቤቶችና ተቋማት እንዲውለበለብ እንደሚደረግ ተገልጿል። የምክር ቤቱ አባል አቶ ሙክታር መሃሙድ የቀደመውን ሰንደቅ ዓላማ ህዝቡ የሚያውቀው በመሆኑ ለውጥ መደረጉ አግባብነት እንዳለው ተናግረዋል። የሰንደቅ ዓላማው ወደ ቀደመ መልኩ መመለስም መሪዎች በተለዋወጡ ቁጥር እንዳይቀየር የማድረግ አሰራርን አስፈላጊነት እንደሚያመለክት ጠቁመዋል። ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚለውን የክልሉን ስያሜ በመቀየር "የሶማሌ ክልል" በሚል እንዲገለጽ ወስኗል።